በሲዳማ ክልል ግብር ከፋዮች በታማኝነት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል- አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ፤ መስከረም 19/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የገቢ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ  የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አሳሰቡ ።

"ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ የታክስ ህግ ተገዢነት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል ።


 

በዚሁ ጊዜ ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልል መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር  ተግባራት በአግባቡ በማከናወን ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የግብር ገቢ ወሳኝ ጉዳይ  መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ያሉት የገቢ አማራጮች ተተንትነው ግብር በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ አመልክተው፤ በየዓመቱ ግብር የመክፈልና ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች የማከናወን አቅም እንዲያድግ ግብር የመሰብሰብ  ተግባር መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።

ክልሉ ከተደራጀ ጀምሮ ከህዝቡ ጋር በተቀናጀ መንገድ ባደረገው  ርብርብ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ያመለከቱት አቶ ደስታ፣ይህንንም ለማድረግ የተቻለው ከዜጎች በሚሰበሰብ የገቢ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።

ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ለክልሉ ልማት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ ፈጣን ልማቶች በሁሉም ዘርፎች በማስመዘገብ  ሕዝቡን ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

በቀጣይም ይህን አጠናክረን በመቀጠል የህዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል አበክረን እንሰራለን ሲሉ አሰታውቀዋል። 

በየዓመቱ ክልሉ የግብር መሰብሰብ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ አሁንም ካለው አቅም አንጻር ገና የሚቀር በመሆኑ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ ጉዱራ፤ በክልሉ ባለው  አቅም ልክ ገቢ ለመሰብሰብ በተደረገው ጥረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተው፤ ለአብነትም የክልሉ ገቢ ማሰባሰብ አቅም በየዓመቱ 31 በመቶ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን 40 በመቶ ወጪ በራስ ገቢ መሸፈን መቻሉን ጠቁመዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት  ደግሞ 13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን ወጪ 60 በመቶ ለመሸፈን መታቀዱን አመላክተዋል።

ውጤቱ የሚያስደስት ቢሆንም ክልሉ መሰብሰብ ከሚገባው የገቢ አቅም አንጻር ግን ብዙ ስራዎች እንዳሉ ያመለክታል ብለዋል። 

በክልሉ ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች ዘመናዊ የታክስ ስርዓት ያለመዘርጋት፣ ግብርን በፈቃደኝነት የሚከፍል  አነስተኛ መሆን፣ የግንዛቤ ችግር፣ የክፍያ ደረሰኝ ያለመቀበል፣ ህገወጥ ንግድ መበራከትና ሌብነት መሆናቸውን አመላክተዋል።

ባለስልጣኑ  ችግሮች ለመፍታት በዋናነት ግንዛቤ ማሳደግና የህግ ተገዥነትን ማጠናከር ላይ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም በክልሉ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጨምሮ ግንባር ከፋዮችን ያካተተ ዘጠኝ አባላት ያሉት የግብር አምባሳደር በመሾም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

በዕለቱ የግብር አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት መካከል የሀዋሳ ህይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢ ፓስተር ጌቱ አያሌው ፤ ግብር መክፈል መጽሀፍ ቅዱሳዊና የክርስትና ስነምግባር የሚያዝዘው ዕሴት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ማድረግ ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን አንስተው፣ ከሚያገኘው ግብርን መክፈል ለራሱም ሆነ ለሀገር በረከት ነው ብለዋል።

እርሳቸውም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት  ማህበረሰቡ ግብርን በአግባቡ እንዲከፍል ተግተው እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል።

የይርጋለም ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ባለቤት ወይዘሮ ይርጋለም አስፋው በበኩላቸው፤ ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ በመሆን በተከታታይ ዓመታትና ዛሬም  መሸለማቸው አንሰተው፤ ለሀገር ዕድገት የሚውለውን ግብርን ከምናገኘው በታማኝነት መክፈል ይገባል ብለዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ  በ2015 በጀት ዓመት ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ የሆኑ ተቋማት እንዲሁም የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰራተኞች የዕውቅና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም