ለድሬዳዋ ልማት በገንዘብ የሚደረገውን ድጋፍ በቀላሉ ለማሰባሰብ የሚያግዝ ሶፍትዌር እና ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

160

ድሬደዋ፤ መስከረም19/2016(ኢዜአ)፣- ለድሬዳዋ ልማት በገንዘብ የሚደረገውን ድጋፍ በቀላሉ ለማሰባሰብ የሚያግዝ ሶፍትዌር እና ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሶፍት ዌር እና "ሄልፕድሬ ዶት ኮም" የተሰኘው የገቢ ማሰባሰቢያ ድረ ገጹ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ የድሬዳዋ የልማት ተባባሪዎች ካሉበት ሆነው ድጋፋቸውን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችላቸው በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የድሬዳዋ ወዳጅና ተወላጅ የሆኑ ባለሙያዎች አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ለሚያከናውናቸው ተግባራት አጋዥ እንዲሆን የሰሩትን ሶፍት ዌርና ድረ ገፅ ዛሬ ለአስተዳደሩ ከንቲባ አስረክበዋል።

በድሬደዋ አስተዳደር የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን እና የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባራትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ከንቲባው ከድር ጁሃር ተናግረዋል።


 

 "ቻፓ የፋይናንስ ተቋም" ላበረከተው ቴክኖሎጂ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቴክኖሎጂው የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የድሬዳዋን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ከያሉበት የጀመሩትን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

"የድሬዳዋን ማህበራዊ ችግሮች በራሷ ልጆችና ተወላጆች የመፍታቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት ከንቲባ ከድር፣ በድረ ገጹ የሚሰበሰበው ሃብት ለትምህርት ቤት ምገባና በድሬዳዋ በተደራጀው የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ነፃ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚውል ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ በዘንድሮ ዓመት በድሬዳዋ የሚከናወኑ የምጣኔ ሃብትና የማህበራዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶች እንዲሁም የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በቁርጠኝነት ይሰራል።

ሶፍትዌር እና የገቢ ማሰባሰቢያ ድረ ገፅ ፈጠራውን ለአስተዳደሩ ያስረከበው ቻፓ የፋይናንስ ተቋም ስራ አስኪያጅ ወጣት እስራኤል ጎይቶም በበኩሉ እንደተናገረው፣ ለድሬዳዋ ሁሉን አቀፍ ዕድገትና የነዋሪውን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ተቋሙ በዕውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል።


 

በስነስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህን ጨምሮ የካቢኔ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም