ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የ2016 የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የ2016 የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ
ነቀምቴ ፤መስከረም 19/2016 (ኢዜአ)፦ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የ2016 የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ።
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘመኑ ከ17ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከመጀመሪያ ዲግሪ ሁለተኛ ዓመት እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ባሉት ደረጃዎች ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተመላክቷል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መልካ ሂካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ነባር ተማሪዎቹን መስከረም 21 እና 22 ቀን 2016 ለመቀበል ዝግጅት አድርጓል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ የሚቀበለው በነቀምቴ፣በሻምቡና በጊምቢ ካምፓሶቹ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዘንድሮውን የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር ለተማሪዎች በቂ የማረፊያ፣የመማሪያና የመመገቢያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ዶክተር መልካ አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በክፍል ከሚያገኙት እውቀት በተጨማሪ በጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲያጎለብቱ ይሰራልም ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራር ዶክተር ከፍያለው ዋቅቶሌ በበኩላቸው፤ ተቋሙበትምህርት ዘመኑ 17ሺህ 322 ነባር ተማሪዎቹን በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮቹ ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ከሚከታተሉት የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ያሉትን ተማሪዎቹን በቀጣዩ ሣምንት መጀመሪያ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ለምዝገባ በተመደቡት ቀናት በየካምፓሶቻቸው በመገኘት ምዝገባቸውን እንዲያከናውኑ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ሬጂስትራሩ አስረድተዋል።