በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምቱ የተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትን በበጋ ወራት ማስቀጠል ይገባል ---ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምቱ የተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትን በበጋ ወራት ማስቀጠል ይገባል ---ቢሮው
ዲላ ፤ መስከረም 19/ 2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምት ወቅት የተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትን በበጋ ወራትም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አሳሰበ።
በክልሉ ጌዴኦ ዞን "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መዝጊያና የበጋ ወራት የአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ማርቆስ ማቲዮስ በወቅቱ እንዳሉት፣ በክልሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን የማህበረሰቡ ባህል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል።
በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች በተካሄደ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ከ119 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ 6 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ መቻሉንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለአረጋዊያንና ለአቅመ ደካሞች ከ3 ሺህ 256 በላይ ቤቶችን ግንባታና የመጠገን ሥራ መከናወኑን አቶ ማርቆስ ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ በአገልግሎቱ ከ7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከመንግስትና ከህዝብ ይወጣ የነበረ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል።
"በአገልግሎቱ የተገኘው ውጤት መደጋገፍ ካለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የተመዘገበው ውጤት በበጋ ወራትም በመድገም የኅብረተሰቡን ችግሮች ለማቃለል መስራት እንደሚገባም ሃላፊው አሳስበዋል።
በጌዴኦ ዞን በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የበርካቶችን ሕይወት መቀየራቸውን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።
መሰረታዊ በሚባሉ ዘርፎች በተለይ በቤት ግንባታ፣ በደም ልገሳና በማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም በችግኝ ተከላ የተገኙ ውጤቶች በዞኑ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች የማይናቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
"የወጣቶችን ተሳትፎና ስኬቶችን ከማጠናከር ባለፈ የመረዳዳት ባህላችንን በማጎልበት በዞኑ ድህነትን ለመቀነስ መስራት አለብን" ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች የዞኑን ሰላም አጠናክሮ በማስቀጠል፣ በግብርና እና በሌሎች መስኮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩም አስገንዝበዋል።
የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደግነት ሃይሉ በበኩላቸው፣ በዞኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከወጣቶች ባለፈ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እና በተቋማት ዘንድ እየተለመደ መምጣቱን ገልጸዋል።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 292 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ በተሰሩ ልማቶች ከ685 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በልማት ስራው ከ1 ሺህ 400 በላይ ቤቶች ግንባታና ጥገና፣ ከ350 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ እንዲሁም በርካታ የበጎ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ በማህበረሰቡ ዘንድ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህልን ከማዳበር በተጨማሪ የበርካቶችን ሕይወት ትርጉም ባለው መልኩ መቀየሩን አቶ ደግነት ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ የላቀ አገልግሎት ላበረከቱ አካላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የዞኑ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ወጣቶች እና የጌዴኦ አባገዳን ጨምሮ የባህልና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።