የብርቅዬዎችን አምባ በዩኔስኮ መዝገብ ላይ እናቆይ! 

በመሐመድ ረሻድ

ባሌ ሮቤ(ኢዜአ)
 
ኢትዮጵያ የብዙ ሕብረ ብሔራዊ ባህልና ማንነት ያሏቸው ሕዝቦች ሀገር ነች። የተፈጥሮ ገፅታዋ በልዩነት ውስጥ አንድነትን፣ በብዝሃነት ውስጥ ህብረትን አጎናጽፏታል። ከህዝቦቿ ጥምር ውበት ባለፈ ተፈጥሮ ያደላት የበርካታ ጸጋዎች ባለቤትም ናት። መስራት የሚገባውን ያክል ሳይሰራበት ቢቆይም አሁን ላይ እነዚህን ተፈጥሯዊ ሃብቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነትም ለማሳደግ እየተሰራባቸው ይገኛል።


በዚህ ረገድ ሥሙ በቀዳሚነት ጎልቶ የሚነሳው ባለብዙ የተፈጥሮ ውበት ባለቤት የሆነውና "አንድ ፓርክ ብዙ ዓለማት (One Park Many World)" ተብሎ የሚታወቀው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው። 
 
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሌ ዞን የሚገኘው ይህ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በ411 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለው ይህ ስፍራ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚያሰኝ ሃሴትን የሚሞላ ግርማ ሞገስን የተላበሰ ነው። 


 


ፓርኩ በሀገራችን ከሚገኙ 27 ብሄራዊ ፓርኮችና ሌሎች ጥብቅ ደን ስፍራዎች አንዱ ነው። በውስጡ በርካታ የብዝሃ-ህይወት ሃብትን የያዘና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ነው።  የደጋ አጋዘን፣ቀይ ቀበሮ፣ትልቁ ፍልፈል፣ የሳነቴ አምባ፣ የሀረና ጥቅጥቅ ደን ፓርኩ ከሚታወቅባቸው ብርቅዬዎች መካከል በዋነኞቹ ናቸው። 
 
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ2 ሺህ 150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ተከልሎ የተመሰረተው በ1962 ዓ.ም ሲሆን በውስጡ ከ1 ሺህ 600 በላይ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች፣ ከ78 ዓይነት በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት እና 300 የሚደርስ ዝርያ ያላቸው አዕዋፍን ይዟል። ከነዚህ መካከል 32 የእጽዋት ዝርያዎች እና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ 31 ብርቅዬ የዱር እንስሳት እንደሚገኙበትም ከብሔራዊ ፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ጥቂት ስለ ብሔራዊ ፓርኩ ጸጋዎች፦


 
⦁    የሰማይ ላይ ደሴት(The Island in the Sky) - የሳነቴ አምባ
 
የሳነቴ አምባ የተፈጥሮ ድንቅ ስራ የሚታይበት የፓርኩ ልዩ ገፅታ የሚንፀባረቅበት ነው። ስፍራው በአፍሪካ ካሉት ፕላቶዎች በስፋቱ 17 በመቶ የሚሸፍን ሜዳማና ትልቁ የአፍሮ አልፓይን አምባ ወይም የሰማይ ላይ ደሴት(The Island in the Sky) ነው፡፡ ይህ ውርጫማ ስፍራ የከፍተኛ ተራራዎች መገኛ ሲሆን፤ በሀገራችን በከፍታው ሁለተኛ የሆነውና ከባህር ጠለል በላይ 4ሺህ 377 ሜትር ከፍታ ያለው የቱሉ ዲምቱ ተራራ መገኛም ነው፡፡ 
 
የሳነቴ አምባ ከመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ባሻገር የዝናብ ውኃን የመሰብሰብና የማጥራት አቅም ያለው ድንቅ መልክዓ ምድር ነው። በተለይ በአካባቢው የሚገኙ የባሌ ፍልፈሎች ከጠላቶቻቸው ለማምለጥ ሲሉ የሚሰሯቸው እልፍ ጉድጓዶች ውኃው ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ ከፍተኛውን ሚና ይወጣሉ። ይህም ከ40 የሚበልጡ ጅረቶች ከፓርኩ እንዲፈልቁ ምክንያት ሆኗል። ጅረቶቹ አቅማቸውን በማሰባሰብ እንደ ዋቤ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዌልመልና ዱማል የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞችም መነሻ ቦታ ነው፡፡  ከዚህ የተነሳ ሳነቴ የ'ውኃ ጋን' የሚል ስያሜንም እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል። 
 
ከሳነቴ አምባ የሚፈልቁት እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በዞኑ የደሎ መናና ሀረና ወረዳ ለሚገኙ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የዘመናዊ መስኖ ልማት ምንጭ እየሆኑም መጥተዋል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የግንባታ ሥራውን ከሶስት ዓመት በፊት ያስጀመሩትና ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ከ11 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ  የማልማት አቅም ያለው የዌልመል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጄክት አንዱ ማሳያ ነው። 
 
ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያና ሶማሊያ የሚኖረው ከ30 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህልውው ከዚህ አካባቢ በሚፈልቁ ተፋሰሶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን በብሔራዊ ፓርኩ የዱር እንስሳት ክትትልና የምርምር ቡድን መሪ አቶ ሴና ገሼ ያስረዳሉ። 
 
⦁    "የሀረና የተፈጥሮ ደን ሀብት" 
 
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ  በሀገራችን በጥቅጥቅ ደን ሽፋኑ ከያዮ ደን ቀጥሎ የሁለተኛነትን ስፍራ የያዘው የሀረና የተፈጥሮ ደን ሀብት መገኛም ነው፡፡ ደኑ የፓርኩን 1ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሸፍናል፡፡ ከሀገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለካርቦን ንግድ ታጭተው ህብረተሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን እያገዙ ከሚገኙ የሀገራችን ድንቅ ደኖች ውስጥም አንዱ ሆኗል። 
 
የሀረና የተፈጥሮ ደንን በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር አርሶ አደሩን በ38 የደን ማህበራት በማደረጃት ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች ከ179 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከከርቦን ንግድ ሽያጭ መገኘቱን በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዕቅድ ክትትል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቀነዓ ያደታ ይገልጻሉ። 



 
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ባሉት የእጽዋት እና የእንስሳት ብዝሃ ህይወት ሲታይ ከዓለም በ34ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ በ12ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ፓርኩ በውስጡ ከሚገኘው እጽዋትና የእንስሳት ብዝሃ ህይወት በተጓዳኝ ለአዕዋፍ ዝርያ ካለው ምቹ ሁኔታ የተነሳ “Bird Site International” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት "በዓለም ከሚገኙ ምቹ የአዕዋፍ መገኛዎች አንዱ ስለመሆኑም አብነቱን ይሰጣል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከላይ የተጠቀሱ እውናታዎችን ጨምሮ ሌሎች የፓርኩ እምቅ አቅሞችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እ.ኤ.አ. በ2009 በጊዜያዊ መዝገቡ ላይ ማስፈሩም ይታወሳል። 
 
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ በርካታ ባለድርሻ አካላት ባለፉት ዓመታት ቅርሱ በቋሚነት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የፓርኩ ኃላፊ አቶ ሻሚል ከድር ያስታውሳሉ። በተለይ ፓርኩ በድርጅቱ በቋሚ የቅርስ መዝገብ ላይ እንዳይሰፍር ማነቆ ሆነው ከቆዩት መካከል ልቅ ግጦሽ፣ የሰደድ እሳት፣ ህገ ወጥ ሰፈራ ሲሆኑ፤ ችግሮቹ አሁንም ያልተሻገርናቸውና የሁሉንም ትኩረት የሚሹ ናቸው ይላሉ።
በተለይ በፓርኩ አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው ሰደድ እሳት የብርቅዬ የዱር እንስሳትን መኖሪያና ምግባቸውን ስለሚያሳጣቸው በቀጣይነት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ያስረዳለሁ።
 
⦁    "ፓርኩን ለማቆየት የተከፈለ የህይወት መስዋዕትነት" 
 
ይህ የብርቅዬዎች አምባ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በተላይም የባሌ ህዝብ፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አያሌ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በተለይ በ2007 ዓ.ም ፓርኩ ላይ ተነስቶ የነበረው የሰደድ እሳት በባሌ ህዝብ ዘንድ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ነው አቶ ሻሚል ያስታወሱት።  
 
በግንዛቤ ማነስ ጭምር ግለሰቦች ለከብቶቻቸው የተሻለ መኖ ለማግኘት በማሰብና ለማር ቆረጣ በፓርኩ ክልል ውስጥ እሳት በመለኮስ ያስነሱትን ቃጠሎ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ለማጥፋት ጥረት ሲያደርግ ህይወቱን ያጣውን የፓርኩን ሰራተኛና የአካባቢ ተቆርቋሪ  ወጣት ቢኒያም አድማሱን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ወጣቱ የተፈጥሮ ሀብት ጀግና በሚል በፓርኩ ውስጥ የማስታወሻ ሀውልት ቆሞለታል። እንዲሁም በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባካሄደው ዓመታዊ ግምገማ የተፈጥሮ ሀብት ጀግና ለሆነው ለቢኒያም አድማሱ ቤተሰቦች ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።
 
እንዲያም ሆኖ ግን ጠባሳው በብዙ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ነው፡፡ ይህ በብዝሃ ህይወት ስብጥሩና በአያሌ ጸጋዎች የተንበሸበሸው የብርቅዬዎች አምባ በቅርቡ በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ተካሂዶ በነበረው 45ኛው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ታላቅ የተፈጥሮ ቅርስና በዓለም ደግሞ 11ኛው ቅርስ በመሆን በቋሚነት መመዝገቡ ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች አስደስቷል። 
 
ፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለቅርሱ የሚደረግለትን ጥበቃ ለማጠናከርና መስህብነቱን ለመጨመር እድል እንደሚፈጥር የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሮብዳ ጃርሶ ይገልጻሉ።  እንዲሁም ፓርኩ በዩኔስኮ እውቅና ማግኘቱ የቱሪስት ፍሰቱን በማሻሻል ከቱሪዝም የሚገኘውን ዓመታዊ ገቢ በማሳደግ ሀገርና ሕዝብ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር ነው ይላሉ። ቅርሱን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሮብዳ ህብረተሰቡ ተንከባክቦ ለዛሬ ያቆየውን ቅርስ በዘላቂነት መጠበቁ ላይ እንዲበረታም  አሳስበዋል። 
 
በፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ሰው ሰራሽ ጫና ሊቀነሱ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ገቢራዊ እያደረጉ ከሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መካከል የፍራንክፈርት ዞሎጂካል ሶሳይቲ ድርጅት የባሌ ዞን ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አብዱርቃድር ኢብራሂም የፓርኩ የጥበቃ ሥራ የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፈ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ። በተለይ በፓርኩ አጎራባች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በፓርኩ ላይ እያደረሱሷቸው ያሉ ጫናዎችን ለመቀነስ ህይወታቸውን የሚመሩበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጽዕኖውን መቀነስ እንደሚቻል ያምናሉ። ፓርኩን በዩኔስኮ ቋሚ መዝገብ ላይ ለማስፈር የተደረገው የተቀናጀ ጥረት እንዳለ ሆኖ ይሄው ገጽታውና ክብሩ ተጠብቆ እንዲቆይ ከፍተኛ ጥረትና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅም በአጽኖኦት ያስረዳሉ። 
 
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ነፊሳ መሐመድ እንዳሉት ፓርኩን ለመጎብኘት ለሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኝዎች የዕደ ጥበብ ቁሳቁሶችን በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸውን እየመሩ ናቸው። እንደሳቸው እምነት በአሁኑ ወቅት ፓርኩ በቋሚነት በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ ለቅርሱ የሚያደርጉትን ጥበቃ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው። 



 
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በአካባቢ ሳይንስ ላይ ምርምር የሚያደርጉት አቶ አልይ መሐመድ እንዳሉት በፓርኩ አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፓርኩ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ቢሆኑ የጥበቃውን ሥራ በእጅጉ ያቃልላል የሚል እምነት አላቸው። ይህ ደግሞ የባለቤትነት ስሜትን በሚፈለገው ደረጃ እንዲያዳብሩ የሚያደርግም ነው። 
 
በመሆኑም በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመቀነስ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከብሔራዊ ፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮች ተጠቃሚ በማድረግ የባለቤትነት አስተሳሰብን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። በተለይ ለማህበረሰቡ አማራጭ የግጦሽና የሰፈራ ቦታ፣ የማገዶ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች አማራጮች በቀጣይ እንዲቀርቡለት የማድረግ ስራ ቢሰራ በፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ጫና ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንደሚቻልም ይመክራሉ። 
 
ከሀገር አልፎ የዓለም ቅርስ የሆነውን የብርቅዬዎች አምባ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ ቋሚ መዝገብ ውስጥ ለማቆየት የሚያግዙ ሥራዎችን ከወዲሁ አቅደው እየሰሩ መሆኑን የፓርኩ ኃላፊ አቶ ሻሚል ያስረዳሉ።  ብሔራዊ ፓርኩን በሚያዋስኑ ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለብዝሃ ህይወት ጥቅምና ተጓዳኝ ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ አግኝተው በጥበቃው የድርሻቸውን እንዲወጡ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማዳበሪያ ሥራዎች  እየተከወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል። 
 
የዓለም ቅርስ የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወትን በዘላቂነት መንከባከብና መጠበቅ የሚያስችሉ ሀገር በቀልና ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ፓርኩን በድርጅቱ ቋሚ መዝገብ ውስጥ ከማቆየት ባለፈ ከዘርፉ የሚገኘውን ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን በቁርጠኝነትና በፅናት ሊወጣ ይገባል። 
 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም