በተደረገልን እገዛ ወደ ቀደመ የእርሻ ስራችን እንድንመለስ አስችሎናል -የአበርገሌ ወረዳ አርሶ አደሮች

125

ሰቆጣ ፤መስከረም 19/ 2016(ኢዜአ)፡- በተደረገላቸው የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ድጋፍ ወደ ቀደመ የእርሻ ስራቸው  እንዲመለሱ እንዳስቻላቸው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር  አበርገሌ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ። 

በነበረው ችግር ተፈናቅለው የነበሩና በመልሶ ማቋቋም ወደ መደበኛ የግብርና ስራቸው በተመለሱ አርሶ አደሮች የለማ ሰብል በመስክ ተጎብኝቷል።


 

በጉብኝቱ ወቅት በወረዳው ነዋሪ   አርሶ አደር ገብረ ፃዲቅ ሃበነ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤  በነበረው ችግር ምክንያት  ከቄያቸው ተፈናቅለው  በመጠለያ ጣቢያ ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል። 

የነበረው ችግር እየተቃለለ በአካባቢያቸው ሰላም በመስፈኑ ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን አመልክተው፤  በመኸሩ ወቅት በተደረገላቸው የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ድጋፍ ዳግም ወደ ግብርና ስራቸው መግባታቸው  ገልጸዋል። 

መንግስት ድጋፍ ባያደርግልን ይህንን የሰብል ልማት አናይም ነበር  ያሉት አርሶ አደሩ ፤ አሁን ላይ ያለሙትን ሰብል እየተንከባከቡ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 አርሶ አደር ሞገስ እምባዬ በበኩላቸው፤ በተደረገላቸው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ዳግም ወደ ግብርና ስራቸው እንዲመለሱ እንዳስቻላቸው አስረድተዋል። 

በወቅቱ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የመግዛት አቅም እንዳልነበራቸው አስታውሰው፤ በተደረገላቸው  ድጋፍ ችግራቸው መቃለሉን  አስታውቀዋል። 

ከአንድ ሄክታር በሚበልጥ መሬታቸው ''እንቁ'' የተሰኘ ዳጉሳ በማልማት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ችግሩ ተቃሎላቸው ተስፋቸው መለምለሙን ገልጸዋል። 

የአበርገሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ወልደየስ በወቅቱ እንዳሉት፤  በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በወረዳው  አርሶ አደሮች ጨምሮ ከ37ሺህ በላይ   የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ነበር።  

ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰው፤ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር አርሶ አደሩን የመልሶ ማቋቋም ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል። 

በዚህም  ለአርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። 

የተደረገው ድጋፍም አርሶ አደሮቹ ከጠባቂነት ወጥተው  ምርታማ ሆነው እራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በነበረው ችግር  ምክንያት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር  31 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ከምርት ውጭ ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ በዛብህ ጌታሁን ናቸው። 

ወደ ቄያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮችን ወደ ቀደመ ግብርና ልማት እንዲመለሱ 585 ኩንታል ምርጥ ዘር መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መቅረቡን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ወደ ቀደመ የግብርና ስራቸው እንዲመለሱ ማስቻሉን ጠቁመዋል። 

ድጋፍ ካደረጉት መካከል የ "ሄልቬታስ ኢትዮጵያ ካርድ ቱ ፕሮጀክት"  አስተባባሪ አቶ አምላኩ አበበ እንዳመለከቱት፤  3 ነጥብ 6 ሚሊዮን  ብር ወጪ በማድረግ 150 ኩንታል የማሾና "እንቁ"  ዳጉሳ ምርጥ ዘር  ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ተችሏል።

ወደ ቀያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከሰብል ልማት ባሻገር በዶሮ እርባታ ለማሰማራት ድርጅቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም