የመከላከያ ሰራዊቱ የአገርን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው- ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን 

223

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የመከላከያ ሰራዊቱ የአገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ገለጹ፡፡

በመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነትና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች ዛሬ አስመርቋል። 


 

ተመራቂዎቹ በኮሌጁ ቆይታቸው የወገንን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡና የጠላትን እንቅስቃሴ መግታት የሚያስችላቸውን ክህሎትና ሙያ ማግኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን፤ የውጊያ መሃንዲስ ዋነኛ ተልዕኮ የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ መሰናክሎችን በማስወገድ የሰራዊቱን እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታቸው ያገኙትን የንድፈ ሃሳብና የተግባር እውቀት በመጠቀም የዕለት ተዕለት ስራዎቻቸውን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡  

በሰለጠኑበት ሙያ የአገርን ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝብን ደኅንነት በመጠበቅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማይፈልጉ የውጪ እና ውስጥ ኃይሎች የሚቃጡ ጥቃቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት አፍራሽ ተልዕኳቸውን መቀልበሱን ገልጸዋል።

አንዳንድ አካላት የሀገር ማፍረስ ቅዠታቸውን ለማስፈጸም የሰራዊቱን ስም ለማጥፋትና በሀሰት ለመከፋፈል ያልሞከሩት ነገር እንደሌለ በመጥቀስ፤ ሰራዊቱ በፅናት፣ በአንድነትና በጀግንነት ሴራቸውን አክሽፏል ብለዋል።

ሌተናል ጀነራል ይመር አክለውም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነትና የህዝቧን ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ኪታባ ሂንሰርሙ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኮሌጁ የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ እየሰራ ነው።  

የዛሬ ተመራቂዎችም በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነት እና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ በንድፍና በተግባር የታገዙ ሥልጠናዎችን መከታተላቸውን አብራርተዋል። 

የወታደራዊ ምህንድስና ሙያ ተመራቂዎች በበኩላቸው፤ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው የሰራዊቱን ተልዕኮ የመፈፀም አቅም ለመጨመር እንደሚሰሩ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ 

ሻለቃ ተስፋዬ ዘውዴ በኮሌጁ ቆይታቸው ባገኙት እውቀት አገራቸውን በብቃት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና በሙያዊ ስነምግባር ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ምክትል አስር አለቃ ጤናው አሰሙ ናቸው።

በመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በ1934 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአምስት የትምህርት መስኮች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም