በዱብቲ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ሥራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዱብቲ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ሥራ እየተሰራ ነው

ሰመራ ፤መስከረም19/2016(ኢዜአ)፡- የዱብቲ ከተማን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝ ለማድረግ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዲብቲ ከተማ ለሦስት አስርት ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች እንጨት በመሆናቸውና በእርጅና ምክንያት በንፋስ እየወደቁ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ከማድረግ ባለፈ ለወጪ ሲዳርጉ ቆይተዋል።
ጽህፈት ቤቱ ያረጁ የእንጨት ምሰሶዎችን ወደ ኮንክሪት ምሰሶ በመቀየርና መሰረተ ልማቶችን በማሻሻል ችግሩን ለመፍታትና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደስራ መግባቱን አስታውቋል።
የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን ዓሊ ለኢዜአ እንዳሉት ያረጁ የእንጨት ምሰሶዎች ትራንስፎርመር መሸከም እያቃታቸውና በንፋስ ሀይል በተደጋጋሚ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጭምር በመውደቅ ጉዳት በማድረስ ተቋሙን ለካሳ ክፍያ ሲዳርጉት ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ የመልሶ ግንባታና የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በዱብቲ ከተማ የህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ያሲን ገለጻ በፕሮጀክቱ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት ምሰሶ ከመተካት ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ ሃይል ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች እንዲዳረስ እየተሰራ ነው።
ኘሮጀክቱ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ሰሆን፣ ገንዘቡም ለኮንክሪት ምሰሶ፣ ለትራንስፎርመር፣ ለሰው ሀይልና ሌሎች መሰል ወጪዎች የታያዘ መሆኑን አስረድተዋል።
በኘሮጀክቱ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት ከመቀየር በተጨማሪ 12 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ እና 55 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአነስተኛ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
በተጨማሪም 33 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ 34 ነባር እና 5 አዳዲስ ትራንስፎርመሮች ተከላና ማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው አቶ ያሲን ያስረዱት።
ባለፈው ዓመት የአይሳኢታ ከተማን በተመሳሳይ የኢሌክትሪክ ምሰሶዎችን የመቀየር ሥራ መሰራቱን ያስታወሱት ሥራ አስፈፃሚው፣ ከሦስት ወር በኋላም በአዋሽ ከተማም የእንጨት ምሰሶዎችን ወደ ኮንክሪት የመቀየር ሥራ እንደሚጀመር አመልክተዋል።
በዱብቲ ከተማ የሚኖሩት አቶ ኪዳኔ በዛብህ እና አቶ ተስፋ ደጉ እንደተናገሩት ቀድሞ የነበረው የእንጨት ምሰሶ ሀይለኛ ንፋስና ዝናብ በመጣ ቁጥር እየወደቀ ለአደጋ የሚያጋልጥበት ሁኔታ ይስተዋል ነበር።
በአሁኑ ወቅት እንጨቱ በኮንክሪት ምሰሶ መቀየሩ ይህን አደጋ ከማስቀረት ባለፈ የሀይል መቆራረጥ ችግርን በማስቀረት ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ጽህፈት ቤቱ ከህብረተሰቡ ጋር በተወያየበት ወቅት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች መፍትሄ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በህክምና ዘርፍ የተሰማሩት አቶ የሱፍ ኡመር በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በምሰሶ መውደቅ ምክንያት ሃይል ሲቋረጥ ላልተገባ ወጪ ሲዳረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሚሰጡት የሕከምና አገልግሎት እንዳይቋረጥ በማሰብ ለሚጠቀሙት ጄኔተር ተጨማሪ ወጪ ያወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ የመልሶ ግንባታና ማሻሻል ሥራው ይህን ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው ተናግረዋል።
በዚህ ኘሮጀክት የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል አሊ መሀመድና ጓደኞቹ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ህብረት ሽርክና ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አሊ መሐመድ በበኩሉ፣ በማህበሩ ከተደራጁ ወጣቶች በተጨማሪ ለሌሎች ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።
የመልሶ ግንባታና ማሻሻል ስራው በተያዘው አመት ሲጠናቀቅ የኃይል መቆራረጥ ችግርን በዘላቂነት ከመፍታትም ባለፈ የኃይል አቅርቦቱ ጥራት ያለውና አስተማማኝ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።
በተደጋጋሚ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች እየቀረበ ያለውን ቅሬታ በዘላቂነት ለመፍታት ፕሮጀክቱ አስፈላጊ መሆኑም ነው የተገለጸው።