የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ በዘርፉ ያለውን ትብብር ማጠናከር ይገባል - የቀጣናው አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ በዘርፉ ያለውን ትብብር ማጠናከር ይገባል - የቀጣናው አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በዘርፉ የሰው ኃይል ልማትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የቀጣናው አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በግጭት አፈታትና ሰላም ማስከበር መስክ በሁለተኛ ዲግሪ ከሰሞኑ ማስመረቁ ይታወሳል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የኬኒያ፣ የዩጋንዳና የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ይገኙበታል።
ተመራቂ መኮንኖቹም በቆይታቸው ኢትዮጵያ ለዘመናት ያካበተችውን ስኬታማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በዘርፉ የሰው ኃይል ልማት ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
በኬንያ የአገር መከላከያ ሰራዊት የአየር ኃይል ባልደረባ ሌተናል ኮሎኔል ጂኦፈረይ የጎ፤ በቆይታቸው ያገኙት እውቀትና ክህሎት የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት በራስ አቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ ያገኙት የግጭት አፈታትና ሰላም ማስከበር ሙያም የሚያጋጥሙ ቀጣናዊ የሰላምና ደኅንነት ችግሮችን በትብብር ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ አታሼ በኢትዮጵያ ብርጋዴር ጄኔራል ጃክ አንጎክ ደንግ፤ የትምህርት እድሉ ኢትዮጵያ በሲቪልና በወታደራዊ የሰው ኃይል ግንባታ ዘርፍ ለደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለይም በሰላምና ደኅንነት ሙያ እየተሰጡ የሚገኙ የትምህርትና ስልጠና መስኮችም የቀጣናውን አገራት የሰላምና ደህንነት ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች አገራትም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወሳኝ ሚና እንዳላት ገልጸው ከዚህም ልምድ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዩጋንዳ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዋና መምህር ሌተናል ኮሎኔል ዋታሳ ዴቪድ፤ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጤታማነት የካበተ ታሪክ አላት ብለዋል።
ለአብነትም በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሶማሌና ደቡብ ሱዳን አብዬ ቀጣና የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በብቃት በመወጣት ከፍተኛ ልምድ ያካበተች አገር እንደሆነች ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ልምድም የአገራቸው ወታደራዊ አቅም ለማጎልበት እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ፆታዊ እኩልነትን በማረጋገጥ ብቁ ሴት ወታደራዊ መኮንኖች ለማፍራት እያደረገች የሚገኘው ጥረት ለቀጣናው አገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለአህጉራዊ የሰላምና ደህንነት ትብብር መጎልበት እንደሚሰራ አረጋግጧል።