የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የድሬደዋን አየር ንብረት ለኑሮና ለሥራ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው--ቢሮው

ድሬደዋ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀግብር የድሬደዋን የአየር ንብረት ለኑሮና ለሥራ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

በድሬደዋ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለመትከል ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች 94 በመቶ የሚሆኑት ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኤሊያስ አልይ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመርሀግብሩ የመጀመሪያ ዙር አራት ዓመታት በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን የዛፍ እና የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል።

ከተተከሉት ችግኞች 70 በመቶዎቹ የጸደቁ ሲሆን ችግኞቹም በገጠር በቤተሰብ ደረጃ የተጀመረውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።

"በተለይ የተተከሉ ምርጥ የፓፓያ፣ የጊሽጣ፣ የአንበሾክ፣ የብርትኳን፣ የመንደሪን፣ የአፕል እና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች አፍርተው ለገጠሩ ማህበረሰብ ተጨማሪ ገቢና የተመጣጠነ ምግብ እያስገኙ ናቸው" ብለዋል።


 

በተጨማሪም ለድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ መነሻ በሆኑ ወረዳዎች በቅንጅት የተተከሉት ችግኞች ጎርፍን በመቀነስና ውሃን ለልማት በማዋል የጎላ አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል።

"የአረንጓዴ አሻራ ከጎረቤት ጅቡቲ ጋር ያለንን ሁለንተናዊ ጠንካራ ትስስር ይበልጥ እንዲያብብ እያገዘ ነው" ያሉት አቶ ኤሊያስ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ140 ሺህ በላይ ችግኞች ለጅቡቲ በመላክና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ትስስሩ እንዲጠናከር መደረጉንም ገልጸዋል።

ዘንድሮም በቀጣይ ጥቅምት ወር 100 ሺህ ምርጥ ችግኞችን ለጅቡቲ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ነው አቶ ኤሊያስ ያመለከቱት።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች የድሬደዋ አየር ንብረት ለሥራና ለኑሮ ምቹ ማድረጉን ገልጸዋል።   

በተጨማሪም ነዋሪዎች ችግኝ ተክሎ መንከባከብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ይበልጥ እንዲገነዘቡ አድርጓል ብለዋል።

አቶ ማስረሻ እንዳሉት በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ለመትከል ከተዘጋጁት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 94 በመቶ የሚሆኑት ተተክለዋል።

አሁን በአካባቢው እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ቀሪዎቹ  እንደሚተከሉም አመልክተዋል።

የተተከሉትን ችግኞች ከመንከባከብ በተጨማሪ በክረምቱ ተተክለው በተለያዩ ምክንያቶች ያልበቀሉትን መልሶ የመተካት ሥራ እንደሚሰራም አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።

ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ለድሬዳዋ ነዋሪዎች የህልውና ጉዳይ መሆኑን በአፅንኦት የተናገሩት ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ አገር አቀፍ የድሬዳዋ ተሸላሚው አቶ በያን ምትኩ ናቸው። 

በደን መመናመን ምክንያት ጎርፍ ከ17 ዓመታት በፊት በድሬደዋና በነዋሪዎቿ ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ አደጋ አስታውሰዋል። 

አምና በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ በአንድ ጀንበር 880 ሺህ ችግኞች ሲተከሉ የአረንጓዴ አሻራ አርበኛው  አቶ በያን በሺዎች የሚገመቱ ችግኞችን ተክለው በመንከባከብ ታሪካዊ ሥራ ሰርተው አርአያ ሆነዋል።  


 

"ሁሉም የድሬደዋ ነዋሪዎች ችግኞችን ተክለው በመንከባከብ አካባቢያቸውን መለወጥ አለባቸው" ሲሉም አስገንዝበዋል።

በድሬደዋ አስተዳደር በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ከ12 ሚሊዮን በላይ የጥላ፣ የፍራፍሬ እና የዛፍ ችግኞች ይተክላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም