አቶ እያሱ ወሰን ለአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው ቀረቡ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኢትዮጵያን በመወከል እጩ ሆነው ቀረቡ። 

ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጥቅምት 2/2016 ኮንፌዴሬሽኑ በደቡብ አፍሪካ ደርባን እንዲካሄድ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚከናወን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ኢትዮጵያን በመወከል በምርጫው እንዲሳተፉ ፌዴሬሽኑ መርጧቸዋል። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢያሱ ወሰን ምርጫው አህጉር አቀፍ ስፖርትን ለመምራት የሚደረግ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኮንፌዴሬሽኑ አባላት ለአፍሪካ የቦክስ ስፖርት ትክክለኛ የሚበጀውን ሰው መምረጥ አለባቸው ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ምርጫው የኢትዮጵያን የቦክስ ስፖርት ገጽታ ለመቀየር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ለምርጫው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአቶ እያሱ በተጨማሪ የኮንፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አዛንዚያ ኦሞ-አጌጌ ከናይጄሪያ፣ የዩጋንዳ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሞሰስ ሙሃንጊ፣ በርትራንድ ሜንዱጋ ከካሜሮን እና መሐመድ ኤል ካቡሪ ከሞሮኮ ይወዳደራሉ።

ከቀረቡት እጩዎች የተሻለ ድምጽ ያገኘው ተወዳዳሪ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመሆን ለአራት ዓመት ያገለግላል። 

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ 50 አባል አገራት አሉት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም