የሆራ አርሰዲ ኃይቅን ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የማልማት ሥራ በዚህ ዓመት ይጀመራል 

128

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት የሆራ አርሰዲ ኃይቅን ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የማልማት ሥራ በዚህ ዓመት እንደሚጀመር የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።    

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት የሆራ አርሰዲ ኃይቅን ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው። 


 

የማልማት ሥራው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ዓመት የ150 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መነሻ በጀት ተይዞለታል ነው ያሉት። 

ፕሮጀክቱ የሆራ አርሰዲ ኃይቅ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኚዎች ዓመቱን ሙሉ የሚዝናኑበትና የኃይቁን ዙሪያ የበለጠ ሳቢ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የልማት ፕሮጀክቱ በዋናነት የመሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች፣ የማስዋብ ሥራና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን ያካተተ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል።    

የፕሮጀክቱ ዲዛይን እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው የልማት ፕሮጀክቱ ከአካባቢው ተፈጥሮ ጋር የሚጣጣምና ኃይቁን ለመጠበቅ የሚያግዝ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ጎብኝዎች የሚዝናኑበትና ወደ ከተማ የሚመጡ የጎብኚዎች ፍሰትም ለመጨመርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም