የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነትና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ ያሰለጠናቸውን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነትና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ ያሰለጠናቸውን አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- በመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነትና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች አስመረቀ።
የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ኪታባ ሂንሰርሙ በዚሁ ጊዜ ኮሌጁ የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ተመራቂዎቹ የወገንን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥና የጠላትን እንቅስቃሴ መግታት የሚያስችላቸውን ሙያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በተዋጊ መሃንዲስ አመራርነት እና በተዋጊ መሃንዲስ መሰረታዊ ሙያ የሰለጠኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ በኮሌጁ አራት ወራት ቆይታቸው የክፍል ውስጥና በተግባር የታገዘ ሥልጠናዎችን መከታተላቸውን አብራርተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፤ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሰልጣኞችም በሰለጠኑበት ሙያ የአገርን ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝቦችን ደኅንነት በመጠበቅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ በ1934 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአምስት የትምህርት መስኮች የተለያዩ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።