በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት ላይ ያተኮረ አህጉር አቀፍ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጉባኤ መስከረም 21 እና 22/2016 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ጉባኤውን ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት(ጂአይዜድ) እንዲሁም ‘አይ ካፒታል’ እና ‘አሶሴሽን ፎር ታለንት ዲቨሎፕመንት’ ከተሰኙ ተቋማት ጋር በትብብር ማዘጋጀቱን ጠቅሷል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጉባኤው በሰው ኃይል ልማት የሚሰሩ የመንግስታት፣ የግሉና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
ዓለም አቀፍ የስራና ክህሎት ገበያ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችል መድረክ መሆኑንም አመልክተዋል።
መድረኩ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ለሚታዩ ክፍተቶች መፍትሔ ለማበጀት እንዲሁም የኢንዱስትሪና የትምህርት ተቋማት ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው ነው የጠቆሙት።
በጉባኤው የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች የሰው ኃይል ስልጠናን ጨምሮ በዘርፉ ለተጀመሩ የለውጥ ስራዎችና ለቀጣይ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
በተለይም ለውጭ አገር የስራ ስምሪት ስራዎች አጋዥ የሆኑ ግብአቶችን ለማግኘት እንደሚያስችል በመግለጽ።
የስራ ፍላጎትና አቅርቦት፣ ከትምህርት ወደ ስራ ሽግግር፣ ዲጂታላይዜሽን ለስራና ክህሎት ያለው እድልና ፈተና፣ የኢንዱስትሪና የትምህርት ተቋማት ትስስር፣ በሰው ኃይል ልማት የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና እና የቀጣይ የዓለም የስራ ሁኔታ አዝማሚያ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡም አመልክተዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የአፍሪካና የሌሎች አገራት የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በስሩ ያሉ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ አጋር አካላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።