በጃፓን የቡና ዓውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ተግባር ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በጃፓን የቡና ዓውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ተግባር ተከናወነ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 18/2016(ኢዜአ)፦ በጃፓን በተካሄደው አለምአቀፍ የስፔሻሊቲ ቡና ዓውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ተግባር መከናወኑ ተገለጸ።
የጃፓን ስፔሻሊቲ ቡና ማህበር (SCAJ) እ.ኤ.አ. ከመስከረም 27 እስከ 29 ቀን 2023 ባዘጋጀው ዓመታዊ የስፔሻሊቲ ቡና ዓውደ ርዕይ በ Tokyo Big Sight የኤግዚቢሽን ማዕከል የተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ንቁ ተሳትፎ መደረጉም ተገልጿል።
በመክፈቻው ዕለት በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ከሌሎች ቡና ላኪ ሀገራት አምባሳደሮችና የስፔሻሊቲ ቡና ማህበር ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን ፕግራሙን አስጀምረዋል።
በዚህ አለምአቀፍ ትዕይንት በኤምባሲውና በኢትዮጵያ ቡና ማህበር አስተባባሪነት የአገራችንን ቡና የማስተዋወቅ ተግባር እንዲሁም ባህላዊ የቡና አፈላልና የስፔሻሊቲ ቡና ጣዕም ቅምሻ መካሄዱ ተጠቅሷል።
ከማኅበሩ በተገኘው መረጃ ከ30 ሀገራትና አካባቢዎች የተውጣጡ ቡና፣ ምግብና መጠጥ ጋር የሚገናኙ 250 ካምፓኒዎችና 45 ሺህ የሚጠጉ ጎቢኚዎች በኤግዚቢሽኑ የተሳተፉ መሆኑንና በኢትዮጵያ በኩልም ከ45 በላይ ቡና አምራቾችና ላኪዎች መሳተፋቸው ተመላክቷል።
በዚህም ከጃፓን ቡና ገዥ ካምፓኒዎች ጋር የማስተዋወቅ ተግባራት መከናወኑ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያን ቡና ከማስተዋወቅ በተጓዳኝ ከኢትዮጵያ ወደ ጃፓን የሚገባውን የቡና መጠን ለማሳደግ አላማ ያደረገ ውይይት ከጃፓን ከፍተኛ ቡና ገዢ ካምፓኒዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር መደረጉ ተጠቅሷል።
በዚህም በአምባሳደር ዳባ ደበሌ የተመራ ልዑክ ከጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ካዙያ ናካጆ ጋር በጃፓን ገብያ የኢትዮጵያን የቡና ገበያ ማሳደግ የሚያስቸል ውይይት መደረጉ ተገልጿል።
ከጃፓን የስፔሻሊቲ ቡና ማህበር (SCAJ) ተወካዮች ጋርም የአገራችን አቻ የቡና ተቋማትና ዘርፉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት በሚችሉባቸውና የኢትዮጵያን የቡና ንግድ ማሳደግ ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም ተጠቅሷል።
በውይይቱ የተሳተፉ የካምፓኒዎች ተወካዮችና የስራ ኃላፊዎች ለተደረገላቸው ገለፃ በማመስገን ከኢትዮጵያ የሚገዙትን ቡና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።