የአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር በክልሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር የሚያስችለውን የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 18 /2016(ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር በክልሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር የሚያስችለውን የሶስትዮሽ ስምምነት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አህመዲን ሙሐመድ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ተፈራርመዋል፡፡

የሶስትዮሽ ስምምነቱ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ዘርፎችን ፋይዳ ያላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመተግበር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የሚተገበሩት ቴክኖሎጂዎች በተለይም በመሬት ዘርፍ ያለውን ህገ-ወጥንነት ለመከላከል፣ ተቋማትን ከብክነት ለመታደግና ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

ይህም የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛል ነው የተባለው፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በዚሁ ወቅት፤ ስምምነቱ በአማራ ክልል ስማርት ሲቲን ለመተግበር፣ ንግድና ገቢዎች ዘርፍን ለማሳለጥና የቱሪዝም ሴክተሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያግዛል ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው በስምምነቱ መሰረት በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፉ ክልሉን ለማገዝ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን ሙሐመድ፤ ስምምነቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ህገ-ወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራ፣ የስራ አጥነትና መሰል ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረትም መሬት ስራን በካዳስተር እንዲመራ በማድረግ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ማዘመን ላይ በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መሰረት ባደረጉ ተግባራትም በተለይ የክልሉን ዋና ከተማን ጨምሮ ሌሎችንም የሴኩሪቲ ካሜራ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም