ብሔራዊ የስፔሻሊቲ ፕሮግራም በህክምና ዘርፍ ፍትሃዊ የባለሙያ ስርጭት እንዲኖር ያስችላል- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የስፔሻሊቲ ፕሮግራም በህክምና ዘርፍ ፍትሃዊ የባለሙያ ስርጭት እንዲኖር ያስችላል- ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 18 /2016(ኢዜአ)፡-የስፔሻሊስት ሀኪሞችን ቁጥር ለማሳደግ የተጀመረው የስልጠና ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ የባለሙያዎች ስርጭት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
በሀገሪቱ የሚታየውን የህክምና ስፔሻሊቲ ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ብሔራዊ የስፔሻሊቲ ፕሮግራም ጀምሯል።
ፕሮግራሙ ከተጀመረ አራት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን የስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሀኪሞች በማዕከል ደረጃ የሚመደቡበትና ፈተና የሚሰጥበት አሰራርንም ይከተላል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈፃሚ አሰግድ ሳሙኤል እንዳሉት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጤና የሰው ኃይል ልማት ላይ በተሰራው ስራ በተለይ በቁጥር ደረጃ በርካታ መሻሻሎች እየታዩ ነው።
ፕሮግራሙ ሲጀመር የህክምና ስፔሻሊቲ የሚሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 8 እንደነበሩ አንስተው አሁን ላይ 19 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ22 የህክምና አይነቶች የስፔሻሊቲ ትምህርት እየሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም በየዓመቱ ከ 1 ሺህ የማያንሱ የስፔሻሊቲ ሀኪሞች ተመርቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ አስረድተዋል።
የባለሙያዎች ምደባ በሚኒስቴሩ የሚካሄድ በመሆኑ በጤና ተቋማት ፍትሀዊ የሆነ ባለሙያዎች ስርጭት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
ፕሮግራሙ በሀገር ደረጃ የሚከናወኑ ከፍተኛ ንቀለ ተከላዎችን ለመስጠት የሚችሉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡
ሰልጠናዎቹን ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ሴና ዱጋሳ፤ ኮሌጁ በተለያዩ መርሃ ግብሮች 67 የህክምና ፕሮግራሞችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።
ከእነዚህ መካከል 20 ዎቹ የስፔሻሊቲ 24ቱ ደግሞ የሰብስፔሻሊቲ መርሃግብሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤
ኮሌጁ ፕሮግራሞቹን ሲቀርፅ የህብረተሰቡን የጤና ችግር በመለየት እንደሆነ አንስተዋል፡፡