በክልሉ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ተገብቷል- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ተገብቷል- ቢሮው

ቦንጋ ፤መስከረም 18/2016 (ኢዜአ) :-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2016 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ ።
በክልሉ ለ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት የመማሪያ ክፍሎች፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውም ተገልጿል።
በክልሉ ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማር ዘርፍ ኃላፊና የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ፣ በ2016 ትምህርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ ምዝገባ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህም ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 13/2016 ዓም ድረስ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የተማሪዎች ምዝገባ ስርዓት በተሳካ ሁኔታ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።
የመማር ማስተማር ሥራው በክልሉ በሚገኙ 1 ሺህ 722 ትምህርት ቤቶች በተደረገው ቅድመ ዝግጅት መሰረት መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም ትምህርት በይፋ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ከበዓላት ጋር ተያይዞ በወቅቱ መጥተው ያለመመዝገባቸው እና የክልል አቀፍ ፈተና ከወሰዱት የማለፊያ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ቁጥር አናሳ ሆኖ መገኘቱ በተወሰነ ደረጃ የተመዝጋቢ ቁጥሩን እንዲቀንስ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል ።
በተቀመጠው ሀገራዊ የትምህርት ማስጀመሪያ ሰሌዳ መሰረት በክልሉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ደስታ አመልክተዋል።
በክልሉ በ2016 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት የሚመዘገብበት ለማድረግ መታቀዱን ገልጸው ለዚህ እንዲረዳ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በክረምት ወቅት ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የሚረዱ የመማሪያ ክፍሎችና የመምህራን መኖሪያን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎች፣ ትምህርት ቤቶችን ማስዋብ፣ የስልጠናና የውይይት ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች ከቀድሞው በተሻለ መልኩ ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ሥራና መምህራንና ተማሪዎች ተሟልተው መገኘታቸውን በማረጋገጥ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር መከናወኑን ገልጸዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን 784 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መታቀዱን የገለፁት የባርታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አስራት ሀይሌ ናቸው።
በታቀደው መሰረት የምዝገባ ሂደት ተጠናቅቆ ከመስከረም 14 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ ወደ መማር ማስተማር ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
በተለያዩ በዓላት ምክንያት መንጠባጠቦች እንዳይኖሩ ወላጆች ተማሪዎችን ሀላፊነት ወስደው እንዲልኳቸውም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የትምህርት አጀማመርን አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የግራዝማች ጳውሎስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሊባኖስ ተመስገን፣ በክረምቱ ትምህርት ቤቱን የማስዋብና ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ የማድረግ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል።
ተማሪዎችን የመመዝገብ ስራ በማጠናቀቅ ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች ውስጥ ዋና ተግባር መሆኑን ጠቁመው፣ ለመመዝገብ በታቀደው መሰረት በማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል ።
ዘንድሮ ትምህርት በአዲሱ ካሪኩለም የሚሰጥ በመሆኑ የሚባክን የትምህርት ጊዜ እንደማይኖር የገለፁት መምህር ሊባኖስ፣ የተማሪ ወላጆችም ይህን በተገቢው ተረድተው ለልጆቻቸው ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ6 መቶ 47 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ መማር ማስተማር ሥራ መግባቱን በትምህርት ቢሮው በኩል ማስታወቁ አይዘነጋም።