የቢሾፍቱን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - የከተማዋ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - የከተማዋ አስተዳደር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 18 /2016 (ኢዜአ)፡-የቢሾፍቱን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የቢሾፍቱ ከተማ በአገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች በብዛት የምትጎበኝ ከተማ ነች።
ከተማዋን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸው እንዲጨምር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የከተማዋን ተፈጥሯዊ መስህቦች በመጠቀም በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እንድትሆን የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በተለይም የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማትና ደረጃቸውን ማሻሻል እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ሥራ በመንግሥትና በግል ዘርፉ አጋርነት የሚከናወን መሆኑን በመጠቆም።
እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች መካከል የአስፓልት መንገድ ሽፋን እንዲሁም የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎትን ተደራሽነት ማስፋት ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት።
በየዓመቱ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ከገጽታ ግንባታ ባለፈ ለከተማዋ ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ 62 ሺህ ሄክታር መሬት የምትሸፍን ሲሆን በሦስት ክፍለ ከተሞችና 10 ወረዳዎች መደራጀቷን የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ያመለክታል።