በሲዳማ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  1 ሚሊዮን 640 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል- የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ

 ሀዋሳ ፤ መስከረም18/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች 1 ሚሊዮን 640 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን  የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ገለፀ።

 በተደረገ እንቅስቀሴም  ከመንግስት ይወጣ የነበረን 722 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉም ተገልጿል። 

የቢሮው ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ለገሰ እንዳሉት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 13 ዋና ዋና ተግባራት ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል።

በእዚህም ከ731 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማቱ ሥራዎችን በማከናወን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን አስታውሰዋል።

እስካሁንም በተደረገ እንቅስቀሴ 722 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ከመንግስት ይወጣ የነበረን ወጪን ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በማህበረሰብ አገልግሎት ከተከናወኑ ስራዎች መካከል የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ ደም ልገሳ፣ የሠላምና ፀጥታ፣ የትራፊክ አደጋ መከላከል፣ ሙያዊ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአረጋዊያን ቤቶች እድሳትና ሌሎችንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ላይ ከ600 ሺህ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ "በተከናወኑ የልማት ሥራዎችም 1 ሚሊዮን 640 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል" ብለዋል;።

ለደም ልገሳ የተለየ ትኩረት በመሰጠቱ ከወጣቶችና ከህብረሰቡ አበረታች ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደስታ፣ በክረምቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 2 ሺህ ዩኒት ደም እስካሁን ድረስ ከ2 ሺህ 500 ዩኒት በላይ ደም በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ለማሳካት እንደተቻለ አስረድተዋል።

አቶ ደስታ እንዳሉት በማህበረሰብ አቀፍ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለበዓል ማዕድ በማጋራት፣ የትምህርት ቁሶችን በመለገስ፣ የወጣት ማዕከላትን በማጠናከርና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ተሳትፈዋል።

"እስካሁንም ከ850 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት በወጣቶች፣ በመንግስት ተቋማትና በሌሎች አካላት ታድሰዋል" ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው ከታደሰላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በይርጋዓለም ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ አማረች በዳኔ አንዷ ናቸው።

በእድሜ ብዛት ለጉዳት የተዳረገችው ደሳሳ ቤታቸው ለጸሐይና ለዝናብ በማጋለጥ ለችግር ዳርጓቸው ሲኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

የቤቱ በርም በእርጅና ተጎድቶ ብዙ ጊዜ ክፍት በመሆኑ ለስርቆት ሲጋለጡ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት ቤታቸው በአዲስ መልክ በመሰራቱ መደሰታቸውን የገለፁት ወይዘሮ አማረች፣ "ከሰሞኑ ደህና እንቅልፍ እየተኛሁ ነው" ሲሉ ቤቱን ለሰሩላቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቀች ኃይሉ በበኩላቸው በህመም ምክንያት ብዙም መንቀሳቀስ ከተሳናቸው ባለቤታቸውና ከአራት ልጆቻቸው ጋር በደሳሳ ጎጇቸው ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በደሳሳ ቤታቸው ንፋስ፣ ዝናብ እና ጎርፍ በቀላሉ ይገባ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ በብሎኬት የተገነባ ያማረ ቤት ተሰርቶ በመረከባቸው እፎይ ማለት መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በሲዳማ ክልል በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ካሉ ወጣቶች መካከል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወጣት እድላዊት አበራ በበኩሏ፣ "በጎ ሥራ ፈጣሪንና ሌሎች ሰዎችን የምናስደስትበት እኛ ደግሞ የህሊና እርካታን የምናገኝበት ትልቅ ፀጋ ነው" ብላለች።

ከእነሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶችም መልካም የሆነ ሥነ ምግባርን የሚያወርሱበት ተግባር በመሆኑ ደስ ብሏቸው እንደሚሳተፉ ነው የገለጸቸው።

ከአንድ ዓመት በፊት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰዷን የተናገረቸው ወጣቷ፣ በሀዋሳ መሀል ክፍለከተማ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል ቤተ መጻህፍት ውስጥ ስታገለገል መቆየቷን ገልፃለች።

ቤተ መጻሕፍቱን ለማጠናከር የተለያዩ መጻህፍት መለገሷን ገልጻ፣ በቀጣይም የበጎ ፈቃድ ሥራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጣለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም