በሰመራ ሎጊያ ከተማ ወንጀልን ለመከላከል በማህበረሰብ ተሳትፎ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል--የከተማው ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በሰመራ ሎጊያ ከተማ ወንጀልን ለመከላከል በማህበረሰብ ተሳትፎ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል--የከተማው ፖሊስ

አፋር፤ መስከረም 18/2016 (ኢዜአ) ፡-በሰመራ ሎጊያ ከተማ ወንጀልን ለመከላከል ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ መምጣቱን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ማህበረሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን እያከናወናቸው ባሉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ወንጀል ከመከላከል ባለፈ የተሻለ ደህንነት እየተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ የቀበሌ 04 የማህበረሰብ ፖሊሲንግ አስተባባሪ አቶ መሐመድ አስኑም እና የከተማዋ ፖሊስ አባል አቶ ሳሊህ አህመድ እንዳሉት ቀደም ሲል በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የስርቆት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ነበር።
ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ሌት ተቀን እየተከናወነ ባለው ወንጀልን በጋራ የመከላከልና የጸጥታ ሥራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በእዚህም በከተማዋ ባለፉት ጊዜያት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር በመዋላቸው የሚፈጸም የስርቆት ወንጀል በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡን ከስርቆት፣ ከንጥቂያና ከዘረፋ ወንጀሎች ለመታደግ እየተከናወኑ ያሉ የማህበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በሰመራ ከተማ መስተዳድር ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት የፈዴራሊዝም አስተምህሮ ሥርዓት ቡድን መሪ አቶ መሃመድ ዓሊ በበኩላቸው የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ ለማጠናከር ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ተግባር ማህበረሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ የሥራው አካል ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ በእዚህም ህብረተሰቡን ከጸጥታ አካላት ጋር በማቀናጀት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ የተለያዩ የስርቆት ወንጀሎች ተበራክተው እንደነበር ያስታወሱት ቡድን መሪው፣ ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ባሉ ወንጀልን ቀደሞ የመከላከል ሥራዎች የስርቆት ወንጀል በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የተዋቀረው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲንግ አገልግሎት አባላት የራሳቸውን ሀላፊነት እየተወጡ መምጣታቸው ለተገኘው ውጤት የጎላ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች 950 ሰዎች የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲንግ ስልጠና ወስደው ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የከተማ መስተዳድሩ ሠላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ አብዱ ኢሴ ናቸው።
ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች በከተማዋ ሲስተዋሉ የነበሩ አብዛኞቹ የወንጀል ድርጊቶች እየተፈቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለፖሊስ ተባባሪ ሆኖ በመስራቱ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ህብረተሰቡ ውስጥ እንዳይደበቁ ማድረግ መቻሉንም አቶ አብዱ አስረድተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ከድር ሰይድ በከተማዋ ባለፉት ጊዜያት ተደጋጋሚ ስርቆቶች ሲፈጸሙ እንደነበር አስታውሰው፣ "በአሁኑ ወቅት ህዝብን በማሳተፍ እየተከናወኑ ባሉ የወንጀል መከላከል ሥራዎች የሰላም እንቅልፍ እየተኛን ነው" ብለዋል።
ፖሊስ እና ማህበረሰቡ በቅንጅት እያከናወኑት ባለው ሥራ በከተማዋ ቀድሞ የነበረው የሌብነት ወንጀል እየቀረ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ ወጣት ሱሌ አሊ እና አብደላ ሁመድ ናቸው።
"ተከታታይነት ያለው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲንግ ስራ በመሠራቱ የስርቆት ወንጀል ጭራሽ ቆሟል ማለት ባይቻልም ቀንሷል፤ የተሻለ ሰላምና እፎይታ አግኝተናል" ብለዋል።
በዋናነት በባጃጆች የታገዘ የስርቆት ወንጀል ይካሄድ እንደነበረ አስታውሰው የተቀናጀ ሥራ በመሰራቱ በአሁኑ ወቅት ወንጀል በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።