በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ምክንያት  ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

ጋምቤላ ፤ መስከረም 18 /2016(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሶች  ድጋፍ ማድረጉን  አስታወቀ።

በማህበሩ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቼንኮት ዴቪድ ፤ ማህበሩ ድጋፉን ያደረገው ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በአምስት ወረዳዎች አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠማቸው 475 እማወራዎችና አባወራዎች መሆኑን በድጋፍ ርክክብ ወቅት ገልጸዋል።


 

ከድጋፉ ውስጥ ብርድ ልብስ፣ የመኝታና የዝናብ መከላከያ ፕላስቲክ፣ የውሃ ጄሪካንና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ ድጋፉን ማሰራጨት መጀመሩንና ቀሪዎቹን እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲልም  ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ተመሳሳይ ድጋፍ ለ725 እማዎራዎችና አባዎራዎች መደረጉን አስታውሰው፤ ማህበሩ ሰብዓዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡሞድ ኡሞድ ፤ ማህበሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱ  ፈጥኖ በመድረስ  እያደረገ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በክልሉ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የወንዞች ውሃ ሙላት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማህበሩ  ያደረገው ድጋፍ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  

ጎርፍ ባስከተለው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን የመደገፉ ተግባር በሌሎችም ተቋማት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 

በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቤታቸው ፈርሶ ለችግር መጋለጣቸውን የገለጹት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ፒተር ኡፓቲ ናቸው። 

የቀይ መስቀል ማህበር ያደረገላቸው ድጋፍ በተወሰነ ደረጃ ችግራቸውን እንደሚያቃልላቸው ጠቁመው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ወይዘሮ ተዋበች ብርሃኑ በበኩላቸው፤  የባሮ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰስ በቤትና ንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። 

በቀይ መስቀል ማህበሩ የተጀመረው ድጋፍ በሌሎች ድርጅቶችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በጋምቤላ ክልል ባሮን ጨምሮ ሌሎችም ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ባስከተሉት ጎርፍ በጋምቤላ ከተማ አስተዳደርና በዘጠኝ  ወረዳዎች  ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ቀደም ብሎ ተገልጿል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም