በኮይሻ ፕሮጀክት ያገኘነው እውቀትና ልምድ በቀጣይ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው-የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኮይሻ ፕሮጀክት ያገኘነው እውቀትና ልምድ በቀጣይ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው-የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሰራተኞች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2016 (ኢዜአ)፦ በኮይሻ ፕሮጀክት ያገኘነው እውቀትና ልምድ በቀጣይ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን በኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በተለያየ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎቸ ገለጹ፡፡
ከሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ጎብኝቷል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው በፕሮጀክቱ በተለያዩ የስራ መስኮቸ የተሰማሩ ባለሙያዎች በፕሮጀክቱ ነገ ለሚገነቡ ሌሎች መሰል የልማት ሰራዎች የሚሆን ልምድ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የጂኦሎጂ ኢንስፔክተር የሆነችው ቤዛዊት ሀይሉ ፕሮጀክቱ ግዙፍ መሆኑን እና በዚሁ ልክ ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልጻለች።
ፕሮጀክቱ በርካታ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር የመስራት እድል የፈጠረላት መሆኑንም ጠቁማለች፡፡
በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ መስራትን በዚሁ ፕሮጀክት ልምድ ማግኘቷን ገልጻ በቀጣይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል አይተንበታል ነው ያለችው።
በስራ ቁጥጥር ላይ የተሰማራችው ኢንጂነር ቤተልሔም አባይነህ በፕሮጀክቱ በንድፈ ሃሳብ ያገኘችውን እውቀት በተግባር ያየችበት መሆኑን ተናግራለች።
በኢትዮጵያ የልማት ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ በሆነው በዚሁ ፕሮጀክት የመስራት እድል በማግኘቷም የተለየ ስሜት እንደፈጠረላት ተናግራለች።
ፕሮጀክቱ በቀጣይነት መሰል ስራዎች ላይ እንዲሰማራ ልምድ ያገኘበት ከመሆኑ ባሻገር ራሱን እንዲችልና ቤተሰቡን እንዲለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገረው ደግሞ ሌላኛው ባለሙያ የሱፍ አባመጫ ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 61 በመቶ መድረሱ መገለጹ ይታወሳል።