አትሌት ትዕግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበችው ውጤት ለተተኪ አትሌቶች መነሳሳትን የፈጠረ ነው-አምባሳደር መስፍን ቸርነት 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2016 (ኢዜአ)፦አትሌት ትዕግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበችው ውጤት ለተተኪ አትሌቶች መነሳሳትን የፈጠረ  መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ፡፡

49ኛውን የበርሊን ማራቶን በድል ላጠናቀቁ አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ዛሬ ማለዳ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተገኝተዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ወቅት፤ ድሉ ማራቶንን ወደ ቀደመ ቤቱ የመለሰ ነው ብለዋል፡፡

የማራቶን ድል የፅናትና የጥንካሬ ምልክት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም በርሊን ማራቶን የተገኘው ውጤትም ኢትዮጵያ ተግዳሮቶችን በልጆቿ በጽናት አልፋ መውጣት እንደምትችል ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ትልቅ ምስክርነትን የሰጠ  መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ውጤቱ ለተተኪ አትሌቶች መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም እንዲሁ፡፡

በዚህም ለአትሌት ትዕግስት አሰፋና ለአሰልጣኟ ገመዶ ደደፎ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም ይብልጥ ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ የተመዘገበው ውጤት  ለፌዴሬሽኑም ሆነ ለአገር ትልቅ ተስፋን የሰጠ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በስራችሁ ኮርተናል፤ እንኳን ወደ ምትወዷት አገራችሁ በድል ተመለሳችሁ በማለት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡   

አትሌት ትዕግስት አሰፋ በበኩሏ በወቅቱ በስፍራው የነበረው የአየር ጠባይ ለመሮጥ ተስማሚ ቢሆንም ከተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክክር እንደገጠማት ገልጻለች፡፡

ነገር ግን በቂ ልምምድ በማድረጌ ክብረወሰን በመስበር ማሸነፍ ችያለሁ ብላለች፡፡

ሌሎች አትሌቶችም ጠንክረው በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉም ነው መልዕክት ያስተላለፈችው፡፡

ሪከርድ ለመስበር በሚደረግ ዝግጅት ትንሽ ስህተት ዋጋ እንደሚያስከፍል በማሰብ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የአትሌት ትዕግስት አሰፋ አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ናቸው፡፡

በ49ኛው የበርሊን ማራቶን አትሌት ትዕግስት አሰፋ በ2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ 53 ሰከንድ ውድድሩን በማጠናቀቅ የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን መስበሯ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም