የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከ45 ሺህ ለሚልቁ ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከ45 ሺህ ለሚልቁ ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ
ዲላ ፤ መስከረም 18/ 2016 (ኢዜአ)፡- የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ከ45 ሺህ ለሚልቁ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማበርከቱን አስታወቀ።
ዩኒየኑ በዞኑ አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ሳቢያ ከትምህርት ቤት እንዳይርቅ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጿል።
በዩኒየኑ የዲላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ክፍሌ አየለ እንዳሉት፤ ድጋፉ በ28 አባል ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለተማሪዎች እየተሰራጨ ነው።
በዚህም በጌዴኦ ዞን ድጋፍ የሚሹ ከ45 ሺህ በላይ የአርሶ አደር ልጆች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ለትምህርት ቁሳቁሶቹ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።
ድጋፉም ደብተር፣ እስክርቢቶና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒየኑ በዞኑ አንድም ተማሪ በደብተር እጦት ሳቢያ ቤት እንዳይውል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን የገለጹት የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው።
ዩኒየኑ የቡና አምራች አርሶ አደሩን የገበያ ችግር በማቃለል የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ ድጋፍ ለሚሹ የአርሶ አደር ልጆች ድጋፍ ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው የተማሪ ወላጆች መካከል አርሶ አደር ኤፍሬም ታደሰ በሰጡት አስተያየት፤ ዩኒየኑ ያደረገው እገዛ ልጆቻችንን በምን እናስተምራለን ብለን እንዳንጨነቅ ያደረገ ነው ብለዋል።