የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 61 መቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 61 በመቶ መድረሱ ተገለፀ።

ከሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን የፕሮጀክቱን አሁናዊ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

የፕሮጀክቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አባይነህ ጌታነህ እንዳሉት በኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ በዓመት 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 6 ተርባይኖች የሚገጠሙለት ሲሆን የተርባይኖች ቤት ፣ የማስተንፈሻ ስራው ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ተጠቅሷል።

እ.አ.አ በ2016 የተጀመረው የፕሮጀክቱ የሲቪል ስራ 52 በመቶ፣ የግድቡ አርማታ ሙሌት 30 በመቶ፣ ማስተንፈሻው 13 በመቶ የደረሰ ሲሆን ኤሌክትሮሜካኒካል ስራው በጥናት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

አጠቃላይ አፈፃፀሙ 61 በመቶ መጠናቀቁን ኢንጂነር አባይነህ አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ለአምስት ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ገድቡ 130 ኪሎሜትር ርዝመት፣ 200 ኪሎሜትር ስኩየር ስፋት የሚሸፍን ሰው ሰራሽ ሐይቅ የሚፈጠር መሆኑም ተመላክቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው የኮይሻ ፕሮጀክት ከተጀመረ ረጂም ጊዜ ካስቆጠሩ እና ትልቅ ትርጉም ካላቸው ሜጋ ፕሮጀክት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ከለውጡ ወዲህ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከሌሎች ፕሮጀክቶች በተለየ የራሱ መልክና ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው ይሄውም ብሔራዊ ፓርኮችን ጨምሮ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ የሚፈጠረው ሐይቅ የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምር መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ፕሮጀክቱን ተከትሎ በሚሰሩ መሰረተ ልማት አውታሮች የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያገናኝ እና አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የአካባቢውን ምርት ለገበያ ተደራሽ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ቱርፋት እንዳለው ተናግረዋል።

የመንግስት የሪፎርሙ ትኩረቶች አንዱ በማድረግ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም