ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ምቹ ከሆኑ 10 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗ ተገለጸ

622

አዲስ አበባ ፤መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ምቹ ከሆኑ10 የአፍሪካ ተመራጭ ሀገራት አንዷ መሆኗን የኦክስፎርድ ምጣኔ ኃብታዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ።

ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2023 ቢዝነስ ለመስራት 10 ምርጥ የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝርን የኦክስፎርድ የአፍሪካ ምጣኔ ኃብታዊ ሪፖርትን ዋቢ አድርጎ ይፋ አድርጓል።

የኦክስፎርድ ምጣኔ ኃብታዊ ሪፖርት “የአፍሪካ ስጋትና ማነቃቂያ መጠቆሚያ” በሚል ርዕስ ገምግሞ 10 አገራትን በምርጥነት አስቀምጧል።

ከአሥሩ አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆና ተመርጣለች።

እነዚህ አገራት ምቹ የንግድ ከባቢ፣ ጠንካራ መሠረተ ልማት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ እንዳላቸው በግምገማ ተረጋግጦ መመረጥ መቻላቸው ተገልጿል።

በተለይ አገራቱ  ምቹ የኢንቨስትመንት ማዕከል መሆናቸው ለዚህ ተመራጭ እንዳደረጋቸውም ዘገባው አመልክቷል።

ሪፖርቱ በእያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ትርፍ እና ኪሳራ፣ የፀጥታ ሁኔታ እና የአፍሪካ ሀገራት ቀጣይ በኢንቨስትመንት የኃብት ፍሰት ምን አንደሚመስል ገምግሟል።

ግምገማው የመካከለኛ ጊዜ የምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ትንበያዎችን፣ የምጣኔ ኃብት መጠንን፣ የምጣኔ ኃብታዊ መዋቅርን እና የሥነ-ሕዝብ አወቃቀርን ያካተተ መሆኑም ተመላክቷል።

የምጣኔ ኃብታዊ ዕድገቱ ጠንካራ በሆነበት የኢንቨስትመንት እድሎች የሚለካ በመሆኑ የምጣኔ ኃብት ዕድገት ምልከታው በግምገማው ላቅ ያለ ክብደት እንደተሰጠውም ተገልጿል።

እነዚህን መስፈርቶች በአብዛኛው አሟልተዋል የተባሉ አሥር የአፍሪካ አገራት መመረጥ ችለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ኮቲዲቯር፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ዩጋንዳ እና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ በምርጥነት በዝርዝሩ ተካተዋል።

ኦክስፎርድ የአፍሪካ ምጣኔ ኃብት መሰረቱን በኦክፎርድ ዩኒቨርስቲ ያደረገ ገለልተኛ የሆነ የምጣኔ ኃብት አማካሪ ድርጅት ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም