በዓላቱ የሰላምና አንድነት ተምሳሌት መሆናቸውን በተግባር እያሳየን ቀጥለዋል- የአክሱምና መቀሌ ነዋሪዎች

አክሱም/መቀሌ፤ መስከረም 17/2016(ኢዜአ)፡-የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላት የሰላም፣ የአንድነትና የመደጋገፍ ተምሳሌት በመሆን አብሮነትን በተግባር ማሳየት የተቻለባቸው ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአክሱምና መቀሌ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ይዘን ለሃይማኖት እኩልነትና ልማት በፍቅርና አንድነትና ልንሰራ ይገባል ሲሉም የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሃላፊ ሼክ አደም ዓብደልቃድር ገልጸዋል።

ከአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ሐጂ መሐመድ ሰዒድ ወሃብ እንደገለጹት፤ የመውሊድ በዓልን ያከበሩት የሌላቸውን ወገኖች በማሰብና ማዕድ በማጋራት ነው።

የዘንድሮ መውሊድና የደመራ በዓላት በተመሳሳይ ቀን መዋላቸው መቻቻል መከባበርና አንድነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

የሁለቱም ሃይማኖቶች ተከታዮች እንደ ቀድሞ ሁሉ በዓላቱ የሰላም፣ የአንድነትና የመደጋገፍ ተምሳሌት በመሆን አብሮነትን በተግባር ማሳየት እንደተቻለባቸውም ገልጸዋል።

ሌላው የአክሱም ከተማ ነዋሪ ቆመስ አባ ዮሐንስ ገብረማሪያም በበኩላቸው፤ በከተማውና አካባቢው የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች የመውሊድና የመስቀል በዓላትን በጋራ በማክበር የቆየ አብሮነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

የመውሊድ፣ ደመራና የመስቀል በዓላት ዘንድሮ በተመሳሳይ ቀን መዋላቸው የሁለቱም እምነቶች ተከታዮች ተቻችለውና ተከባብረው በፍቅር አብሮ የመኖር ዘመን ተሻጋሪ ባህላቸው ይበልጥ ጠንክሮ እንደሚቀጥል አብነት መሆኑን ገልጸዋል።

በመቀሌ የሃወልቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ሃጅ ስዒድ ህሴን የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆኑ፣ አቶ ዳንኤል ዛይድ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ ናቸው።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን የሁለቱንም ሃይማኖታዊ በዓላትን ለ20 ዓመታት አብረው በአንድነትና በአብሮነት አሳልፈዋል።

በጋራ ማክበር ብቻ ሳይሆን ካላቸው ቀንሰው ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ሲደግፉ መቆየታቸውን እና ዘንድሮም ይህንኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ሃይማኖታዊ በዓላትን በጋራ ከማክበር ባለፈ ቤተ-እምነቶቻቸውን በጋራ በመጠገንና በአዲስ በመስራትም ትብብራቸው ጥብቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በአንድ ቀን የተከበሩት የመውሊድና የደመራ በዓላት በጋራ ሲከብሩ በተለያየ መክንያት ለችግር ተዳርገው ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመጠየቅና በማገዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሃላፊ ሼክ አደም ዓብደልቃድር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ይዘን ለሃይማኖት እኩልነትና ልማት በፍቅርና አንድነትና ልንሰራ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

  

 

 

 

 
 

  

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም