የትግራይን የመስህብ ስፍራዎች በአግባቡ በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ፤ መስከረም 17/2016(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም የመስህብ ስፍራዎችንና ቅርሶችን በአግባቡ ጠብቆ በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።

የደመራ በዓል በዓዲግራት ከተማ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በተገኙበት ዛሬ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።


 

አቶ ጌታቸው በዚሁ ጊዜ የተገኘውን ሰላም ተጠቅመን በዓሉን ማክበር እንደቻልነው ሁሉ፤ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን እየጠበቅን የቱሪስት መዳረሻ ልናደርጋቸው ይገባል ብለዋል።

የትግራይ መልሶ ግንባታን ለማፋጠን የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ጌታቸው አረጋግጠዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክብረ-በዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከመንግሥት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም