በሽናሻ ብሄረሰብ ባህል ቂም ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ አይቻልም - የሽናሻ የሀገረ ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሽናሻ ብሄረሰብ ባህል ቂም ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ አይቻልም - የሽናሻ የሀገረ ሽማግሌዎች

አሶሳ (ኢዜአ) መስከረም 17/2016፡- በሽናሻ ብሄረሰብ ባህል ቂም ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ አይቻልም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የብሄረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡
የሽናሻ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል “ጋሪ ዎሮ” በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በድምቀት ተከብሯል፡፡
ከብሄረሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች አቶ ለማ አልጋ እንዳሉት በሽናሻ ብሄረሰብ ቂም ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ አይቻልም፡፡
በዚህም የአዲስ ዓመት እቅድ ከመዘጋጀቱ በፊት የተጣላ ካለ ተፈልጎ እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል ያሉት አቶ ለማ ይህን ተከትሎ የሃገር ሽማግሌዎች ይመርቃሉ ብለዋል፡፡
ሌላው የብሄረሰቡ ሀገር ሽማግሌ አቶ አሰፋ ታዬ በበኩላቸው ከምንም በፊት ለሠላም እና ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት የአባቶቻችን ባህላዊ እሴት ነው ብለዋል፡፡
ያለ ሠላም የሚከናወን ምንም ጉዳይ እንደሌለ ገልጸው፤ የሃሳብ ልዩነትን እንዲከበር ከማድረግ ጀምሮ አለመግባባቶች በግልጽ ንግግር እንዲፈቱ በማድረግ ሃላፊነታቸው እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡
የብሄረሰቡ ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፍ ከተቻለ ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ የሚናገሩት ደግሞ አቶ ተስፋሁን ኪሉ ናቸው፡፡
የብሄረሰቡን ባህል ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍና በተለይ ወጣቱ ትውልድ በውል እንዲገነዘበው ከማድረግ ባሻገር በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነትና ተቀባይነት ተጠቅመው አንድነትንና አብሮነትን ማጠናከር ዋነኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን የብሄረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል፡፡