በአዲስ አበባ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተገነባውን 20ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ በባለሃብቶችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ፣ የእውቀትና የክህሎት ድጋፍ እየተከናወነ መቀጠሉን ገልፀዋል።

የፕሮጀክቶቹ እውን መሆን የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆናቸውን  ከንቲባዋ  ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ለፕሮጀክቶቹ መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ ሁሉ ክብርና ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከንቲባ አዳነች ጠይቀዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሽታዬ መሀመድ፤ ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 20 የምገባ ማዕከላት በተሳካ መልኩ ተገንብተው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ የተሰራው 20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በቶኩማ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ በ47 ሚሊየን ብር ወጪ ነው የተገነባው።

የጉለሌው የምገባ ማዕከል በቀን ከ500 የሚልቁ የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚመግብ መሆኑ ታውቋል።

በአዲስ አበባ እስካሁን የተገነቡት የምገባ ማዕከላት በቀን ከ35 ሺህ በላይ ወገኖችን የምገባ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም