በሀረር ከተማ እና የቻይናዋ ዉሻን ከተማ መካከል የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመሰረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

224

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2016(ኢዜአ)፦በሀረር ከተማ እና በቻይናዋ ዉሻን ከተማ መካከል የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመሰረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት የሀረር ከተማ የጀጎል ቅርስን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ አለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ ናት።


 

ከተማዋ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ከተሞች ብቸኛዋ የአለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት (Organization of World Heritage Cities) አባል መሆኗንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በሰላም ፣ በመቻቻልና በአብሮነት ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን ማግኝቷን ገልጸው ይህም የተለያዩ እምነት ፣ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖሩባት ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ሀረር ከተማ ከቻይና ዉሻን ከተማ ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመሰረት የሚያስችል ፍሬአማ ውይይት ማካሄድ መቻሉን ገልጸዋል።

በውይይቱም ባህልን በማስተዋወቅ ታሪካዊ ቅርሶችንና ሙዚየሞችን በመጠበቅና እንክብካቤ በማድረግ ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙኑትን በማጠናከርና በሌሎችም ጉዳዮች በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የቻይና ዉሻን ከተማ አመራሮች በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ እና በመልካም ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና የልኡካን ቡድናቸው የዉሻን ከተማን እንዲጎበኙም ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም