ለክልሉ ልማት ህዝቡን በማስተባባር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ጀምረናል- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
ለክልሉ ልማት ህዝቡን በማስተባባር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ጀምረናል- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር

መቀሌ፤ መስከረም 17 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡- የትግራይ ክልል ገዚያዊ አስተዳደር ለክልሉ ልማትና እድገት ህዝቡን በማስተባበር መንቀሳቀስ መጀመራቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ጌታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት የክልሉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ሰራ ላይ በማዋልና የህዝቡን አቅም በማስተባበር ክልሉን ለማልማትና ለማሳደግ በትኩረት መንቀሳቀስ ተጀምሯል።
የመስቀል በዓል ከትናንት ዋዜማው ጀምሮ በክልሉ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በመከበር ላይ ይገኛል።
በመቀሌ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው በ”ጮምዓ“ ተራራ ላይ ትናንት በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማው ከንቲባ አቶ ይትባረክ አምሃ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንደገለጹት፤ "ጮምዓ" ተራራን በአግባቡ በማልማት ለቱሪዝም መስህብነት በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ትኩረት ይደረጋል።
ተራራው ለከተማው ውበትና ሳቢነት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ አካባቢውን ለማልማት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፍፁም ነጋሽ በሰጡት አስተያየት፤ "ሰላም ተፈጥሮ የመሰቀል በዓሉን ለማክበር በመቻላችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ሲሉ ገልጸዋል።
ለመቀሌ ከተማ ግርማ ሞጎሰ ባለው” ጮምዓ” ተራራ ላይ የመሰቀል በዓልን በማክበሬ ተደስቼያለሁ ያለው ደግሞ ወጣት ሞገስ መኮንን ነው