የመስቀል ደመራ በዓል ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሊታደሙበት የሚገባ ልዩ ሁነት ነው- የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሊታደሙበት የሚገባ ልዩ ሁነት ነው- የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ በዓል ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሊታደሙባቸው ከሚገቡ ልዩ ሁነቶች መካከል አንዱ ሊሆን ይገባል ሲሉ የተለያዩ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ተናገሩ።
የ2016 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ ወረብ እና ከተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የተወጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ልዩ ልዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል።
በበዓሉ ላይ ከታደሙት የውጭ ዜጎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ አገራት ጎብኚዎች በሁነቱ መደመማቸውንና መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካዊዩ ግራንት ቡሼ፤ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ፍላጎት የረጅም ጊዜ እቅዳቸው እንደነበር ጠቅሰው በመስቀል በዓል ላይ ተገኝተው ድንቅ ነገሮችን በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በእንዲህ አይነት ሁነቶች ላይ ሌሎችም ተገኝተው የኢትዮጵያን ድንቅ ሃብቶች እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልን ገጽታዎች፣ አኗኗርና ትውፊት ቀደም ብለው መጎብኘታቸውን ጠቅሰው እምቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ሃብቶችን በቀጣይነት ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።
ከእንግሊዝ የመጡት ላውሬል ሬይድ፤ እኔ ባለሁበት አገር ስለ መስቀል ደመራ በዓል ብዙ አይታወቅም፤ እዚህ ተገኝቼ በማክበሬና ታሪካዊ ዳራውን በማወቄ ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማኛል ብለዋል።
"እንዲህ ዓይነት ልዩ አጋጣሚ በሕይወት ዘመን አንዴም ቢሆን ልትታደምበት የሚገባ ሁነት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ከቻይና የመጣችው ሌላዋ ታዳሚ ወጣት ሊዩ ኪን፤ በበዓሉ ላይ ስትገኝ የመጀመሪያዋ መሆኑን ገልጻ የበዓሉ አከባበር የሚደንቅና ልዩ ገጽታን የተላበሰ መሆኑን ተናግራለች።
በበዓሉ ላይ አከባበሩ፣ ባህላዊ አልባሳትና እንቅስቃሴዎች ሁሉ አስደንቀውኛል በማለት ገልፃለች።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ 22 ሩሲያዊያን አገልጋዮችም ተሳትፈዋል።