የኢትዮጵያን ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ የጋራ አደራና ሃላፊነት አለብን - አርበኞች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ የጋራ ኃላፊነትና ታሪካዊ አደራችንን መወጣት አለብን ሲሉ አርበኞች ገለጹ።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በርካታ ታዳሚዎችና ቱሪስቶች በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተከብሯል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይም ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ምእመናን እና በርካታ ቱሪስቶች በተገኙበት ተከብሮ ውሏል። 

በከብረ በዓሉ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አባት አርበኛ ሻለቃ ሳሙኤል ለገሰ፤ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶችን ከአገር አልፎ ዓለም እያወቃቸው መጥቷል ይላሉ።

ለዚህም የመስቀል በዓልን ጨምሮ ሌሎችም እሴቶች በዓለም ቅርስነት ተመዘግበው እውቅናቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ የጋራ ሃላፊነትና አደራችንን ለመወጣት መዘጋጀት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።


 

የአርበኛ ልጅ የሆኑት ጽጌ ደምሴ እና ይድነቃቸው ባንታይሙሉ፤ የኢትዮጵዊያን የአንድነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን መጠበቅ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በመሆኑም እነዚህን ሃብቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ በተለይም የኃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰብና ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች ጠብቆ የማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነትና አደራ ሁላችንም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

የመስቀል በዓል የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር መገለጫ ጭምር በመሆኑ በተለይም ወጣቶች ይህንን መልካም እሴት ይዘው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ መጠበቅና መንከባከብ አለብን ሲሉ አርበኞቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵዊያን ቱባ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ትውፊቶች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ የማስማርና ትውልድን የማነጽ ስራም በዘላቂነት መከናወን አለበት ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸው ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች 11 መድረሳቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም