ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር  ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል - የእምነቱ  አባቶች 

አርባ ምንጭ/ሆሳዕና መስከረም 17/2016 (ኢዜአ)፦ ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀልን በዓል ሲያከብር ሰላምንና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የእምነቱ አባቶች አመለከቱ።

የመስቀል በዓል ከዋዜማው ከደመራ በዓል ጀምሮ በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ እንዲሁም በሆሳዕና  በተለያዩ ሃይማኖታዊ ኩነቶች በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋሞ እና የጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሲኖዶሱ አባል ብፁዕ አቡነ ኤሊያስ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀልና የደመራን ተምሳሌት በመከተል አንድነቱንና አብሮነቱን ማስጠበቅ ይገባዋል።

በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በአብሮነት በመታነጽ ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል።

እግዚአብሔር በመስቀሉ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እኛም እርስ በርስ በርህራሄና በፍቅር ልንኖር ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ብፁዕነታቸው።

ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በአልን  ሲያከብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ካለው በማካፈልና በአብሮነት በሰላም፣ በመተሳሰብ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ  ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር የአንድነት ማሳሪያ የሆነውን ፍቅርና ርህራሄ በመላበስና የመስቀልን መርህ በመከተል መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንዲሁም አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ህሙማንን በመጠየቅና አብሮ በመሆን በደስታ ማሳለፍ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

በዓሉን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት ምዕመናንና የበዓሉ ታዳሚዎች እኛ በተሰጠን ፀጋ ስናከብር የእለት ጉርስ ለማግኘት የሚቸገሩ፣ ረዳት የሌላቸው፣ በእርጅናና በህመም ምክንያት ቤት ያሉ ወገኖቻችን በማስታወስ መደገፍ ከፈጣሪም ዘንድ በረከት ያስገኛል ብለዋል።

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው ዲያቆን ረቂቅ ፀጋዬ የአውደ ዓመት በዓላት በተለያየ መንገድ ተራርቀው የነበሩ ሰዎች ከያሉበት አካባቢ በመሰባሰብ የሚያከብሯቸውና የደስታ ጊዜን የሚያሳልፉባቸው ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

በዓሉን በአካባቢያቸው ከሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ጋር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።

ተነፋፍቆ የቆየ ቤተሰብ በጋራ በመሰባሰብ በፍቅርና በደስታ ታጅቦ ከሚከበሩ  በዓላት መካከል አንዱ የመስቀል በዓል ስለመሆኑ የተናገሩት ሌላኛዋ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ንጉሴ ናቸው ።

የመስቀል በዓል አምላክ ለፍቅር ሲል የከፈለውን መስዋዕትነትና ትዕግስት የሚያስተምር መሆኑን አንስተው ይህን  የህይወት  ልምምድ በማድረግ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር እንደሚተጉ ተናግረዋል ።

የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ኢትዮጵያ የኦሮቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክዋኔዎች በደማቅ ስነ ስርአት እየተከበረ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም