የመስቀል ደመራ በዓል ያስገኘውን የአንድነትና የፍቅር እሴቶች በመጠቀም ለዘላቂ ሰላምና እድገታችን ልንተጋ ይገባል--ብፁዕ አቡነ ገሪማ

ዲላ ፤ መስከረም 16 /2016(ኢዜአ)፡-  የመስቀል ደመራ በዓል ያስገኘውን የአንድነትና የፍቅር እሴቶች በመጠቀም ለዘላቂ ሰላምና እድገታችን ልንተጋ ይገባል ሲሉ የጌዴኦ፣ አማሮ ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ተናገሩ። 

የመስቀል ደመራ በዓል በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ሁለገብ ስታዲዬም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ የእምነቱ አባቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ዲያቆናትና ምእመናን የተገኙ ሲሆን በያሬዳዊ ዜማ፣ በስብከተ ወንጌልና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ተከብሯል።

በበዓሉ የታደሙት የጌዴኦ፣ አማሮ ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እንዳሉት የመስቀል በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት ነው።

እኛም ከክርስቶስ ፍቅር በመማር ለወገኖቻችን ፍቅርን፣ ትህትናን እና አንድነትን ማሳየት አለብን ብለዋል።

በተለይም የደመራ በዓል በጋራ ከሆንን ጥንካሬን እንዲሁም ብርሃናችን ጨለማን የሚገልጥ መሆኑን እንደሚያስተምር አስረድተዋል ።

በመሆኑም የመስቀል ደመራ ያስገኘልንን የአንድነት እሴቶች በመጠቀም ለዘላቂ ሰላማችንና እድገታችን ልንተጋ ይገባል ስሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም በዓሉን ሲከበር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመጠየቅና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነ የዓለም ቅርስ ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

በዓሉን መንከባከብ ብሎም ጠብቆ ለትውልድ ማሸጋገር የሁሉም ሃላፊነት መሆን ጠቅሰው "በተለይ ከደመራ እሴቶች በመማር ለሀገር ሰላምና ብልፅግና በጋራ መቆም አለብን" ብለዋል።

በተለይ የሚያለያዩንን ነገሮች በውይይት በመፍታት የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ማውረስ አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በበኩላቸው ደመራ በርካታ ችቦዎችን በአንድ ያስተሳሰረ የመደመር ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑንም ከመስቀል ደመራ ያገኘነውን የሰላምና የአንድነት እሴቶችን በመጠቀም ለከተማችን ሰላምና ሁለንተናዊ እድገት ልንጠቀም ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን እንዲሁም የዞኑ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕና፣ በዲላ፣ በሚዛን አማንና ቦንጋ ከተሞችም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ኩነቶች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም