ብሪክስ ለአፍሪካ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል- ላውረንስ ፍሪማን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ አዲስ የተስፋፋው ብሪክስ ለአፍሪካ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል ሲሉ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን ምዕራቡ ዓለም ከታዳጊው ዓለም በተለይም ከአፍሪካ ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሲተቹ ቆይተዋል።

ፍሪማን ስለ ብሪክስ መስፋፋት እና ለአፍሪካ ይዞት ስለመጣው ዕድል በተመለከተ ከ“Pan African Visions” መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ላውረንስ ፍሪማን በድምር ከ215 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላቸውን ኢትዮጵያንና ግብጽን በአባልነት የተቀበለው ብሪክስ የአፍሪካን አቅም እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

ፍሪማን እንዳሉት አሁን እየተስፋፋ ያለው ብሪክስ ከምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት የተሻለ አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓትን መሠረት ያደረገ ሂደት እየተከተለ ስለሆነ፤ ያልተመጣጠነ የምዕራባውያን የበላይነት ማብቂያ ጊዜ ላይ እንገኛለን።

እ.አ.አ ከጥር 1 ቀን 2024 ጀምሮ የቡድኑ አባል የሚሆኑ ስድስት ሀገራትን ሲጨምር 11 አባል ሀገራት ሲኖሩት፤ ከዚህም ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሶስት ማደጋቸው የብሪክስን ተፅዕኖ እንደሚያሳድግም ነው ተመራማሪው መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ይህ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ እና ለዓለም ልማት በጣም ጥሩ ዜና እንደሆነም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ፣ በምስራቅ አፍሪካ እና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ እድገት የሚያስገኘውን እና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ሊኖራት የሚችለው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው፣ ይህም ለብሪክስ ቀጣይ ተፅዕኖ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በብሪክስ የተቋቋመው እና በመሰረተ ልማት፣ ድህነት ቅነሳ እና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ብድር የሚያቀርበው አዲሱ የልማት ባንክ 30 በመቶ ብድር የሚሰጠው በአገር ውስጥ ምንዛሬዎች መሆኑም ሌላው የብሪክስን አካታችነት እና የዓለም ሥርዓት ለውጥ አይቀሬነት ማሳያ ነው ብለዋል።

ብሪክስ በአጭሩ እንዲቀጭ ምዕራባውያን ሩጫ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ፍሪማን፣ ምዕራባውያን ራሳቸውን ከነባራዊው ዓለም ጋር ከማስማማት ይልቅ ለውጥን ለማኮላሸት የሚያደርጉት ጥረት ለውጡን እንደማያስቀረው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከዘንድሮው የብሪክስ ጉባኤ በፊት የነበረውን የምዕራባውያን ሚዲያዎች ዘመቻ ብሪክስ ጉባኤውን በስኬት እንዳያጠናቅቅ አለማድረጉ በቂ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ብሪክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዓለም ህዝብ 40 በመቶ የሚወክለውን አንድ ሶስተኛ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እንደሚይዝ እና ይህም በርሃብ፣ በኤሌክትሪክ እጦት እና በተለያዩ ጫናዎች እየተሰቃየች ላለችው አፍሪካ መልካም ዕድል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም