የደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ያበረከቱት  አስተዋጽኦ አርያነት ያለው ነው-የባህር ዳር  ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ 

 ባህር ዳር ፤ መስከረም 16 /2016 (ኢዜአ)፡- የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ   ወጣቶች ያበረከቱት  አስተዋጽኦ አርያነት ያለውና ሃላፊነት ከሚሰማው ትውልድ የሚጠበቅ ነው ሲሉ  የባህር ዳር  ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ገለጹ።

የደመራ በዓል በባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ  በሰላም መጠናቀቁን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በወቅቱ እንደገለጹት፤ የደመራ በዓል ተቀብሮ የነበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለማውጣት ስራ የተጀመረበት የሰላም ሥነ-ሥርዓት  ነው።

ይህ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ወጣቱ ሃላፊነት እየወሰደ ሃይማኖታዊ ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።

''የመስቀል በዓል ለክርስትና እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም በዩኒስኮ የተመዘገበ የሀገር ሃብት ጭምር ነው'' ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ናቸው።

በከተማዋ ለሚከበሩ በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በሰላም መጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም የወጣቶች   ዓርያነት ያለው ተግባር ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በባህርዳር በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በርካታ  የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም