ህዝቡ የመስቀል በዓልን ሲያከብር አብሮነቱን በማጠናከር ሊሆን ይገባል- ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል

ጋምቤላ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፡- ህዝቡ የመስቀል በዓልን ሲያከብር አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋምቤላ፣ የአሶሳ፣ የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ገለጹ።

የመስቀል ደመራ በዓል  በጋምቤላ  በድምቀት ተከብሯል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ፤ ምዕመኑ የአንድነትና የአብሮነት እሴት በማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ በዓሉን ማክበር እንዳለበት አመልክተዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የነፃነትና የትብብር እሴት መገለጫ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

 ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ይህኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጋምቤላ ክልል ህዝብ ባለፉት ዓመታት አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር ሰላሙን  በመጠበቅ ረገድ ያሳየውን ቁርጠኝነት በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ምዕመኑ በማህበራዊ የትስስር ገፆች ጥላቻን በመስበክ ሀገርን ለማፍረስ እየተደረገ  ባለው እኩይ ተግባር ሳይታለል ለክልሉ ብሎም ለሀገሩ  ሰላምና ልማት በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሳይመን ቲያች በክብረ በዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ የቱሪስት መስህብ በመሆን  ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት እንዲውል ለሚደረገው ጥረት የከተማው አስተዳደር ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚሰጥ  አስታውቀዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በርካታ የዕምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም