ከመስቀል በዓል አስተምህሮ በመነሳት ሁሉም ለፍቅር፣ ለሰላም እና አንድነት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል -ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶስ

ጂንካ ፤ መስከረም 16 /2016 (ኢዜአ)፡-  "መስቀል ስለፍቅር ለሌሎች ዋጋ መክፈልና ሰላምን አጥብቆ መሻት ስለሚያስተምር ሁሉም ለፍቅር፣ ለሀገር ሰላምና አንድነት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ሲሉ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊጶስ ተናገሩ።

የመስቀል ደመራ በዓል በጂንካ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርአቶች በድምቀት ተከብሯል። 

በዓሉ በከተማው መስቀል አደባባይ ሲከበር የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ስላሴ ካቴድራል መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቡነ ፊሊጶስ በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በእዚህ ጊዜም እንዳሉት የመስቀል በአል ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንድነት እርቅን የሚያስተምር ታላቅ በአል ነው።

በመሆኑም ምዕመናኑ ይህን ታላቅ ክብረ በዓል ሲያከብሩ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

"መስቀል ለሌሎች ማሰብን፣ ስለፍቅር ዋጋ መክፈልንና ሰላምን አጥብቆ መሻትን ያስተምራል" ያሉት አቡነ ፊልጶስ፣ የእምነቱ ተከታዮች ይህንን አስተምህሮ በመከተል መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

የሀገር ሰላም፣ ፍቅርና የህዝቦች ትስስር እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

በዓሉ ያሉት ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል ሲሉም ገልጸዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስፋው ዶሪ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የደመራ በዓል ለሌሎች ዋጋ መክፈልን ስለሚያስተምር አንድነታችንን በእጅጉ ያጎላል ብለዋል።

"በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ከማጠናከር አኳያ ትልቅ ሚና ያለው፣ ሀገራዊ ገጽታን የሚያጎላ እና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ዕንቁ ቅርሳችን በመሆኑ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።

በመስቀል በዓል የሚታየውን  የአንድነት ስሜት በሌሎች የልማት ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል ለአገር እድገት የድርሻን መወጣት እንደሚገባም ተናግረዋል። 

የአሪ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራ በአል የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እሴት ያለው በአል በመሆኑ የበአሉን እሴት አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

ጥልን በማስወገድ በፍቅር፣ በአንድነት እና በመቻቻል ለሀገራዊ እድገት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በበአሉ ላይ የታደሙት የጂንካ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርት እስከዳር አለልኝ፤ የመስቀል በዓል በውስጡ በርካታ ትውፊቶች ያለው ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በአል መሆኑን ተናግረዋል ።

ይህ አኩሪ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴት በዩኔስኮ የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርሳችን በመሆኑ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ እንዲሻገር ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ብለዋል።

በዓሉ የመረዳዳት፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል በመሆኑ ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በመተሳሰብ እና በመረዳዳት እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም