በመስቀሉ ያገኘነውን ድኅነት እያሰብን የሀገራችንን ሠላም ልናስጠብቅ ይገባል- ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ - ኢዜአ አማርኛ
በመስቀሉ ያገኘነውን ድኅነት እያሰብን የሀገራችንን ሠላም ልናስጠብቅ ይገባል- ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ

ወልዲያ/ ደሴ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ) ፡- በመስቀሉ ያገኘነውን ድኅነትና ሠላም እያሰብን የሀገራችንን ሠላም ልናስጠብቅ ይገባል'' ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ዞን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ገለጹ።
በዓሉ በወልዲያ በተከበረበት ወቅት ሊቀ ጳጳሱ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መስቀል የሰላም አዋጅ የታወጀበት በመሆኑ አንዳችን በአንዳችን ላይ ክፉ ሳናወራ በመስቀሉ የተገኘውን ሰላም ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
ሃገር የምትገነባውና የምትቀጥለው በትውልዶች ቀና ትብብርና ትጋት በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት አንዳችን ከአንዳችን ተሽለን በጎ ስራዎችን ልንሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አለማየሁ ካሳሁን በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው እንዳመለከቱት፤ የከተማውን ሰላም በማስቀጠል የተጀመሩ ልማቶች ተጠናቀው የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
የበዓሉ ታዳሚ አቶ ተመቸ ዘውዱ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማችን ሰላም በመስፈኑ ታላቁን የደመራ በዓል በሰላም ለማክበር በቅተናል ብለዋል።
ወይዘሮ ትኩነሽ አስፋው በበኩላቸው፤ የሠላም ዋጋው በገንዘብ የማይተመን የህልውና መሠረት በመሆኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ በዓሉ በደሴ ከተማ ሆጤ ስታዲየም ሲከበር የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መምህራን ብርሃነ ሕይወት እውነቱ ፤ ምዕመናኑ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የመስቀሉን ፍቅርና አንድነት በመስበክ በዓሉን ማክበር አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መስቀሉ ህዝብ ያዳነ የነፃነትና የፍቅር ምልክት ነው፤ ምዕመናኑ በዓሉን ሲያከብር አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ እንደ መስቀሉ ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ኢትዮጵያ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ በዓሉ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት በመሆኑ ሁላችንም ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወጣቱም በሀሰት ትርክት ሳይወዛገብ እውነትን መፈለግና ኢትዮጵያን ለማጽናት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
ሰላማችንን እየጠበቅን በደሴ ከተማ የተጀመሩ ልማቶችን ከማስቀጠል ባለፈ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ልማቶችን ለማከናወን በማቀዳችን ህብረተሰቡ ከጎናችን ተሰልፎ የተለመደ ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
በዓሉን በደስታ፣ በፍቅርና አንድነት በማክበራችን ተደስተናል ያሉት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ አቶ አውራሪስ ደጀኔ ናቸው፡፡
በወልዲያና ደሴ ከተሞች የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተጠናቋል።