ህዝበ ክርስቲያኑ ሰላምና አብሮነትን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት - ብፁዕ አቡነ እንጦንስ 

ጭሮ/አዳማ ባሌ ሮቤ፤ መስከረም 16 /2016(ኢዜአ)፡- ህዝበ ክርስቲያኑ ሀይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱን በመጠበቅ ሰላምና አብሮነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ሐረርጌና የአፋር ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ገለጹ።  

የመስቀል ደመራ በዓል በጭሮ ፣ በባሌ ሮቤና አዳማ ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ተከብሯል።

በጭሮ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ ሲከበር በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን መርዳት፣ መተሳሰብና መከባበርን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ ሀይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱን በመጠበቅ ሰላምና አብሮነትን በተግባር ማሳየቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አሳና መሀመድ በበኩላቸው ፤ በደመራ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ህዝቡ የአከባቢውን ሰላም በመጠበቅና የተቸገሩትን በመርዳት ማክበሩ መጪው ጊዜ ብሩህ ተስፋ ይዞ የሚመጣ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

የከተማው ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲከበር የሀይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ያሳዩት አንድነት የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል  በአዳማ  ከተማ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡፁ አቡነ ጎርጎሪዮስ፤  ችግሮቻችንና በደላችን የተሻረው በመስቀል ነው ፤  አሁንም በሀገራችን  ሰላም እንዲፀና መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መስቀሉ ጥላቻና የጥል ግድግዳን ያፈረሰ፤ ሰላም ፣አብሮነት፣ መቻቻልና አንድነትን ያጎናፀፈን በመሆኑ ከጥላቻና መገፋፋት በመራቅ አንድነትና ፍቅር እንዲያብብ መስራት ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ክንቲባ አቶ ሙላቱ ዲባ ፤ በበዓሉ ላይ  ባስተላለፉት መልዕክት፤  የመስቀል በዓል ሁሉን በእኩልነት የምስተናገደበት ነው፤  ከመስቀሉ ተምረን ለሀገራችን ሰላም በአንድነት መቆም አለብን ብለዋል።

በዚህም ሁሉም በዓሉን ከማክበር ባለፈ የከተማውንና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለሀገር ሰላም በጋራ መቆም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉ በተመሳሳይ በባሌ ሮቤ ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የዕምነቱ ተከታዮችና ሌሎችም እንግደች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። 

በበዓሉ አከባበር  ሥነ ሥርዓት ላይ  ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሮቤና አካባቢዋ ሃገረ ስብከት ፀሐፊ ቄስ ያሬድ ገብረማሪያም ባስተላለፉት መልዕክት፤ መስቀል የአብሮነት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

የደመራ በዓል ራሰን መስጠትን የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ፈተናዎችን በመቋቋም ሀገሩን ማሻገር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮችና የእምነቱ ተከታዮች  ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም