ሕብረተሰቡ የመስቀል በዓልን ሲያከብር በችግር ላይ የሚገኙ ወጎኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል - የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፦ ሕብረተሰቡ የመስቀል በዓልን ሲያከብር  በችግር ላይ የሚገኙ ወጎኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ በተጨማሪ አብሮነትንና የእርስ በርስ መደጋጋፍ የሚገለጽበት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል መምሪያ መምህር አባ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የመስቀል በዓል ስናከብር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ በማጋራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ከተረፈን ብቻ ሳይሆን ካለን ለወገኖቻቸን ማካፈል አለብን ነው ያሉት፡፡

በሸገር ከተማ አስተዳደር የዱከም ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን አስተዳደሪ መጋቢ ሃይማኖት ቆሞስ አባ ገብረ ማሪያም ገብረ መድን በበኩላቸው፣ በዓላትን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ማክበር ኢትዮጵያዊ እሴት ነው ብለዋል፡፡

የተቸገሩትን በመርዳት የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን የመደጋገፍ ባህል ማጎልበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቋሚና ጊዜያዊ ፕሮጀክቶች መምሪያ ኃላፊ መልዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፈ ምዕመኑ ከበዓላት ባሻገር በጎነት ባህል እንዲሆን የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡


 

ከዚህ አኳያ የፍቅርና የአብሮነት ምሳሌ የሆነውን የመስቀል በዓል እርስ በርስ በመደጋገፍ ልናከብር ይገባል ነው ያሉት፡፡

የመስቀል በዓል የሰላም፣የፍቅርና የአንድነት በዓል እንዲሆን የሃይማኖት አባቶቹ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም