የመስቀል ደመራ በዓል በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ እና በድሬደዋ ከተሞች እየተከበረ ነው

ሐረር፣ አሶሳ እና ድሬዳዋ ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፡- የመስቀል ደመራ በዓል በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ እና በድሬደዋ ከተሞች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርአቶች እየተከበረ ነው።

በዓሉን በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት ከማክበር ባለፈ በመስቀሉ የተገኘውን ሰላምና እርቅ እያሰቡ የተቸገሩትን በመርዳት ማክበር እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶች አስገንዝበዋል። 

የደመራ በዓል በሐረር ከተማ መሃል አደባባይ በታላቅ ሀይማኖታዊ ስነ ስርአት እየተከበረ ሲሆን በበዓሉ ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሐረር ከተማና በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የምስራቅ ሐረርጌ ሃገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ኒቆዲሞስ፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ መዘምራን እንዲሁም ህዝበ ክርስቲያኑ በበዓሉ ላይ ታድመዋል።

ለበዓሉ ድምቀት ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ያሬዳዊ ዜማ፣ ሽብሸባና ቅኔ እንዲሁም መዝሙሮችን አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶች ባስተላለፉት መልዕክትም በዓሉን በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሶሳ ከተማም በዓሉ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በዝማሬ፣ በስብከተ ወንጌል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶች እየተከበረ ነው። 


 

በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአሶሳ ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ አምላከፀሐይ አባ አለምነው ፀጋው እንዳሉት፣ በመስቀል ክርስቶስ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ይከበራል።

"በመስቀሉ የተገኘው እርቅ እና ሠላም በሁላችን ልብ ሊኖር ይገባል ብለዋል" ሥራ አስኪያጁ።

"ፈልጉ ይሰጣችኋል" የሚለውን ቅዱስ ቃል መሠረት በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች ሠላምን አጥብቀን መፈለግ ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ወክለው የተገኙት አቶ በድሉ አበራ በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች በማጎልበትና አለመግባባቶችን በማስወገድ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የደመራ በዓል በድሬዳዋም በታላቅ ኃይማኖታዊ እሴቶች በደማቀ ስነስርዓት እየተከበረ ነው።

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን እያከበሩ ያሉት በድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ ተገኝተው ነው።

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ አገረ ስብከትና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

በእዚህም የመስቀል ደመራ በዓልን የተቸገሩትን በመርዳትና የታመሙትን በመጠየቅ እንዲሁም አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ማክበር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የብልጽግና እንዲሆን ምኞታቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ አንድነትና የሀገርን ሰላም በዘላቂነት መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል። 

በበዓሉ ላይ በብዙ ሺህ የሚገመቱ የእምነቱ ተከታዮች፣ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ሊቃውንተ- ቤተክርስቲያናት እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ዘማሪዎች እየተሳተፉ ነው።

በስነስርዓቱ ላይ ዝማሬና ወረብ ከመቅረብ ባለፈ ተቀብሮ የተገኘውን ብርሃነ መስቀል ምንነት፣ ህይወትና ታላቅ የመዳን በረከትን የተመለከቱ መልዕክቶች ተላልፈዋል።

ኢትዮጵያዊ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ ነው።

የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ የቱሪስት መስህብ በመሆን ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም