መንግስት የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ለመጠበቅና ለማልማት ለሚከናወኑ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል- ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ለመጠበቅና ለማልማት ለሚከናወኑ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመስቀል አደባባይ በመከበር ላይ ነው።


 

የባህልና የስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ካሏት ታላላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት አንዱና ዋንኛው የመስቀል ደመራ በዓል ነው።

በዓሉ የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች የተጎናጸፈ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያውያን ዘንድ በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር አመልክተዋል።

መስቀል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ሕዝብ ሃብትና ንብረት ሆኗል ብለዋል።

የመስቀል በዓል ፍቅር፣አብሮነት፣መረዳዳት፣አንድነትና ሰላምን የሚያስተምር መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ

የበዓሉን አስተምህሮ በመከተል በፍቅር አንድ ልንሆንና በሰላም አብረን ልንኖር ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ቀጄላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በትዕግስት፣በንግግርና በይቅርታ በማለፍ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

መንግስት የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁና እንዲለሙ አልፎም ለትውልድ እንዲተላለፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው አቶ ቀጄላ ያመለከቱት።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም