የመስቀል በዓልን ጥላቻና መከፋፈልን በማስወገድ በአንድነትና በፍቅር ልናከብር ይገባል- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፦ የመስቀል በዓልን ጥላቻና መከፋፈልን በማስወገድ በአንድነትና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።

የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን የበዓል መልዕክት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብረሃም አቅርበዋል።

በመልዕክታቸውም መስቀል ድህነትን የሚሰጥ እንዲሁም ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት የሚሰበክበት እንደሆነ ገልጸዋል።

መስቀል በፈጣሪና በሰው ልጆች እርቅ የተፈጠረበት፤ ጥላቻና መከፋፈል የተሸነፈበት መሆኑን አመልክተዋል።

ነገረ መስቀሉ የተለያዩትን የሚያሰባስብ እና የተጣሉትን የሚያስታርቅ የሰላምና የእርቅ ተምሳሌት ነው ብለዋል።

ምዕመናን የመስቀሉን አስተምህሮ በመከተል የፍቅር ምሳሌ የሆነውን በዓል በአብሮነትና በጋራ ማክበር ይገባል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው።

የመስቀሉ ምልክት በሆኑት ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት፣ አንድነትና ይቅርታ መኖር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በክበረ በዓሉ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም