ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናና ህብረ ብሔራዊ አብሮነት መረጋገጥ በአንድነት መነሳትን ከመስቀል ደመራ ልንማር ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፦ከመስቀል ደመራ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እና ህብረ ብሔራዊነት አብሮነት መረጋገጥ በአንድነት መነሳትን መማር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

በስነ-ስርዓቱ ላይም የከንቲባ አዳነች አቤቤን የመስቀል ደመራ መልዕክት የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነጥበባትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው አቅርበዋል።

በመልዕክታቸውም የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ ለተመዘገበበት 10ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል ደመራ ትውፊትን ጠብቃ ለትውልዱ በማስተላለፏና በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጉልህ ሚና በመጫወቷ ምስጋና አቅርበዋል።

መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድህነት ቤዛ የሆነበትና ራሱን አሳልፎ የሰጠበት የፍቅር መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ንግስት እሌኒ የቆሻሻ ክምርን ንደው መስቀሉን ከተደበቀበት ማውጣታቸው ብዙ ያስተምራል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያንና አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ እየተጋን ነው ያሉት በመልዕክታቸው፤ ለዚህ ስኬት የመለያየትና የግጭት ቆሻሻዎችን ማስወገድን ከመስቀሉ ደመራ መማር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በአንድነት በመነሳት ዘመን የማይሽረው ታሪክ መፃፍ እንደሚገባም አስረድተዋል።

የመስቀሉና የደመራ ትውፊት በመዋደድና በመትጋት ልንገልፀው ይገባል ያሉት ከንቲባዋ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የባህል የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነታችን ሲደመር ትልቅ አቅም መሆኑን በመገንዘብ እርስ በእርስ መዋደድን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያንን የህብረ-ብሔራዊ አንድነት እውነታ፣ የልማትና እድገት መሻት ጥረትና ውጤታችንን፣ የነፃነታችን ታሪክን ለመደበቅ ጠላቶቻችን የሚከምሩትን ቆሻሻ ለመናድ በአንድነት መነሳት ይገባል ነው ያሉት።

ከአባቶቻችን የችግር መፍቻ ጥበብን በመማር በመስቀሉ መገኘት የተገለጠውን ትምህርት በምግባር በመኖር አርአያ መሆንም ከሁሉም እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

ለዚህም የፍቅርና የመዋደድን እውነት በየዕለቱ በመግለጥ በመቻቻልና በአብሮነት የኢትዮጵያንና የአዲስ አበባን የሰላም የልማትና የፍቅር ደመራን እንደምር ሲሉም ነው መልዕክታቸውን የቋጩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም