የመስቀል ደመራ  በዓል  ተስፋና ፍቅር ፀንቶ እንዲኖር የምንማርበት ነው - ብጹዕ አቡነ ቀሌምጦስ

93

ደብረ ብርሃን/  ባህር ዳር/  ወልዲያ / ደሴ ፤ መስከረም 16 /2016(ኢዜአ)፡-  የመስቀል ደመራ  በዓል  እምነት፣ ተስፋና ፍቅር በውስጣችን ፀንቶ እንዲኖሩ የምንማርበት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቀሌምጦስ ገለጹ።

በዓሉ በአማራ ክልል  የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በደብረ ብርሃን ከተማ እየተከበረ ባለው  በዓል ላይ  ብጹዕ አቡነ ቀሌምጦስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከቀደምት አበው እንደተማርነው ሃገርን ለመገንባት ፍቅርንና አንድነትን በማብዛት ተስፋን በመሰነቅ በጋራ ፀንቶ በመቆም መሆን አለበት ብለዋል።

የደመራ በዓል ስናከብር እምነት፣ ተስፋና ፍቅር በውስጣችን ፀንቶ እንዲኖሩ የምንማርበት ነው፤ ይህንን  ታላቅ በዓል ስናከብር ካለን ላይ ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ አካባቢያችንን ነቅተን በመጠበቅና በማልማት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የሚስተዋሉ የልማት እድገት ማስቀጠል ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አመልክተው፤ አንድነትንና ሰላምን ለማስጠበቅ ከደመራ መማር እንደሚቻል ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በባህር ዳር ከተማ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።

በክብረ በዓሉ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፣ የባህር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል። 

በአሁኑ ሰዓት በዓሉን  አስመልክቶ በሰባኪያን ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን በበዓሉ የታደሙት የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል።

በወልዲያ ከተማም እንዲሁ የመስቀል ደመራ በዓል  በድምቀት እየተከበረ ነው።

በስነ-ሰርዓቱ የሰሜን ወሎ ሃገረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የታደሙ ሲሆን ፤ በተመሳሳይ በዓሉ በደሴ ከተማ ሆጤ ስታዲዮም በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ከተሞችም እየተከበረ መሆኑ ታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም