የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ እንዳሉት የመስቀል በዓል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የመተባበር፣ የአብሮነት እና የእርስ በርስ መደጋገፍ እሴቶቻችን በጉልህ የሚንፀባረቁበትና ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረ የመጣ በዓል ነው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ በመልዕክታቸው እንዳሉት የመስቀል በዓል የክረምቱ ጭቃ አልፎ ምድር በአበባ አጊጣ፣ በደመና የተጋረደችው ፀሐይ ፈክታ የሚከበር ውብ በዓል ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የመስቀልን በዓል የሚያከብረው በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመተሳሰብ እና በይቅርታ ነው፤ መስቀል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የደስታ በዓል ስለሆነ የዐውደ ዓመት አውራ ተብሎ ይጠራል ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ መስቀል በሀገራችን የተለያዩት ተገናኝተው፣ የተራራቁት ተቀራርበው፣ ዘመድ ከወዳጅ ተሰባስበው የሚከበር የህብር በዓል ስለሆነ ሁላችንም አብሮነታችንን አጽንተን ልናከብረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው እንዳሉት የክረምቱ ወራት አልፎ ምድር በብርሃን ጸዳል ስትደምቅ ከአዲስ ዓመት የእንቁጣጣሽ በዓል በኋላ የሚከተለው ህዝቦች በጉጉት የሚጠብቁት የመስቀል በዓል ይከተላል።

ይህ በዓል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የመተባበር፣ የአብሮነት እና የእርስ በርስ መደጋገፍ እሴቶቻችን በጉልህ የሚንፀባረቁበት እና ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረ የመጣ በዓል በመሆኑ እርስ በርሳችን በመተጋገዝ እና በፍቅር ማሳለፍ አለብን ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለደመራና መስቀል በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የመስቀል በዓል ለረጅም ጊዜ የተራራቁ የቤተሰብ አባላት እና ወዳጅ ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ ወገኖች የሚደገፉበት እና ሌሎች ማኅበራዊ ኩነቶች የሚከወኑበት በዓል ነው ብለዋል።

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ይህን በዓል የባህላቸው፣ የትውፊታቸው፣ የማኅበራዊ ዕሴቶቻቸው አካል አድርገው እንደሚያከብሩት አስረድተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መስቀል የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እንዲሁም የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት እሴታችን ደምቆ የሚታይበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር የሃይማኖቱ አስተምህሮ የሆኑትን አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ ፍቅርና መከባበርን በማስፈን ረገድ ለሁሉም አርአያ ሆኖ በመገኘት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለመስቀል ደመራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ደስታ እንዳሉት መስቀል አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅሩን የገለፀበት፤ ይቅርታንና የኃጢያት ስርየትን ለሰው ልጆች የሰጠበት መለኮታዊ አንድምታ ያለው ሲሆን በመስቀል ፍቅር፥ ሰላም፥ ይቅርታና መተሳሰብ የሚገለፅበት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር የኢትዮጵያዊነታችን ማድመቂያ የእርስ በርስ መዋደዳችን መገለጫ መሆን ይገባል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት መልዕክት በበዓሉ ወቅት የተቸገሩትን በመርዳት ልናከብር ይገባል ብለዋል።

ለዘመናት ተቀብሮ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተጫነው ተራራ ከተደበቀበት ስውር ስፍራ ይወጣ ዘንድ በደመራ ሰማያዊ ምልክት የታየበትን ቀን ለምናከብርበት በዓል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ስገልጽ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ከተለየ አክብሮት እና ፍቅር መልዕክት ጋር ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል በዓል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛ መስቀሉ ከተቀበረበት መገኘቱ የሚታሰብበት በዓል መሆኑን የገለጸው የክልሉ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ በተለዬ ድምቀት የሚከበረው ይህ በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ የዓለምን ማኅበረሰብ ትኩረት በተለዬ ሁኔታ የሚስብ መሆኑ ተጠቅሷል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል በሠላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክርስትና ሃይማኖት አማኞች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል የአገሪቱን መልካም ገፅታ በማጉላት በኩል ፋይዳው የላቀ ነው ። ይህ በዓል የተስፋ፣ የልምላሜና እንደገና በአዲስ መንፈስ ለስራ የምንነሳሳበት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር የሃይማኖቱ አስተምህሮ የሆኑትን አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ መከባበርንና ሠላምን ለሁሉም በማስተማርና አርአያ ሆኖ በመገኘት ነው ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም